ጎርፍ ካጠቃው መኪና አራት ሲሞቱ አንድ ተረፈች
የሥራ ባልደረባውን አድኖ እራሱን ጎርፍ ወሰደው
ሦስቱ የሕክምና ባለሙያዎች ናቸው
Ethiopia Zare (ሰኞ ሚያዝያ 27 ቀን 2000 ዓ.ም. May 5, 2008)፦ ከድሬዳዋ ድልጮራ ሆስፒታል የሕክምና አገልግሎት ለመስጠት ወደ ገጠር ቀበሌዎች ተጉዞ የነበረ የጤና ባለሙያዎች ቡድን ይጓዙበት የነበረው መኪና በጎርፍ ተወስዶ አራቱ እንደሞቱ ሲገመት አንዲት ነርስ መትረፏን የኢትዮጵያ ዛሬ የድሬዳዋ ሪፖርተር ዘገበ።
የሕክምና ቡድኑ ትናንት ሌሊት ወደ ድሬዳዋ በመመለስ ላይ እንዳለ ድሬዳዋ ለመድረስ 17 ኪሎ ሜትር ሲቀረው ለገደኒ በምትባል ቦታ ላይ ነው አደጋው የደረሰበት።
በአካባቢው በተለይ ትናንትና ከፍተኛ ዝናብ ሲዘንብ የነበረ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ባሉ በአብዛኛው አካባቢዎች በትናንትናው ዕለት ዝናብ እንደነበረ ለማወቅ ተችሏል።
በዚሁ በጎርፍ የተጠቃው መኪናው ውስጥ ተሳፍረው የነበሩት ነርስ ፈሪያ አብደላ፣ የጤና ባለሙያ የነበሩት አህመድ ሐሰን እና ጆቫኒ ጥላሁን፣ ሹፌሩ አቶ መሐመድ ሰዒድ እና ሊፍት ሰጥተዋት የነበረችው ነፊሳ ሼህ መሐመድ የተባለች አርሶ አደር እንደነበሩ ለማወቅ ችለናል።
ከእነዚህ ውስጥ ይህ ዜና እስከተጠናከረበት ጊዜ ድረስ በሕይወት የተገኘችው ነርስ ፈሪያ አብደላ ስትሆን፣ አስከሬናቸው የተገኘው የጤና ባለሙያው አህመድ ሐሰን ብቻ ነው። የቀሪዎቹ የሦስቱ አስከሬን በፍለጋ ላይ እንደሆነ ታውቋል።
ነርስ ፈሪያ እንዴት እንደተረፈች በአካባቢው ለእርዳታ ለተገኙ ወገኖች ገልጻለች። ታሪኩ እንዲህ ነው፦ የተረፈችው መኪናቸው በጎርፉ እንደተጠቃች በአቅራቢያው የሚገኝ ዛፍ ላይ ትንጠለጠላለች። አስስከሬኑ የተገኘው የጤና ባለሙያው አህመድ ከተንጠለጠለችበት ዛፍ ላይ ይረዳትና ወደ ዳር ከጎርፉ እንድትወጣ ይረዳታል።
ከዚያም እሷ ተንጠልጥላበት የነበረው ዛፍ ቅርንጫፍ በመያዝ ከጎርፉ ለመውጣት ጥረት በሚያደርግበት ጊዜ ይዞት የነበረው ቅርንጫፍ ይሰበርና መልሶ ጎርፉ ውስጥ ይወድቃል። በዚህን ጊዜ መቆጣጠር አቅቶት ጎርፉ ያሸንፈዋል። አሸንፎም ይዞት ይጓዛል።
በዚህ አይነት ሁኔታ ሕይወቱን እንዳጣ ሕይወቷን ያተረፈላት ነርስ ፈሪያ ለአካባቢው ነዋሪዎች እንዳስረዳች ሪፖርተራችን ካጠናከረው ዘገባ ለመረዳት ችለናል።



