የጉምሩክ ሥራ አስኪያጅ በፖሊስ ተይዘው እንዲቀርቡ ታዘዘ
የፍ/ቤቱ ትዕዛዝ 15 ቀን ቢሆነውም እስካሁን አልቀረቡም
መስሪያ ቤቱ ጉዳዩን በሰበር አሳግዷል
Ethiopia Zare (ቅዳሜ ሐምሌ 12 ቀን 2000 ዓ.ም. July 19, 2008)፦ የኢትዮጵያ ጉምሩክ ባለሥልጣን ሥራ አስኪያጅን ፖሊስ አስሮ እንዲያቀርባቸው ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሰጠ።
በኢትዮጵያ ጉምሩክ ባለሥልጣን 156 ሠራተኞች ያለ አግባብ ከሥራ መታገዳቸውንና ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ በፍርድ ቤት የተሰጠውን ትዕዛዝ ያላስፈፀሙ የባለሥልጣኑ መስሪያ ቤት ሥራ አስኪያጅ በፖሊስ ተይዘው ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ፣ ትዕዛዝ የሰጠ ቢሆንም፤ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ግን ጉዳዩን በሰበር አሳግጄዋለሁ ብሏል።
የባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ ሠራተኞች ያለአግባብ ከሥራ መታገዳቸውን በመግለጽ በፌደራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት ሲከራከሩ የቆዩ ሲሆን፣ መሥሪያ ቤቱም በበኩሉ ሠራተኞቹን የቀነሰው የመዋቅር ማስተካከያ በማድረጉ እንደሆነ በመግለጽ ሲከራከር ቆይቷል።
ፍርድ ቤቱ በሚያዝያ 10 ቀን 2000 ዓ.ም. በሰጠው የፍርድ ውሳኔ፣ ሁሉም የባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ ሠራተኞች የፖሊስ አባላት በመሆናቸውና፣ የአንድ የፖሊስ መደብ ቢሰረዝ እንኳን በመስሪያ ቤቱ ውስጥ ተመሳሳይ የሥራ መደብ መዛወር እንዳለበት የተቀመጠ አስገዳጅ ድንጋጌ መኖሩን በውሳኔው አትቷል።
ስለዚህም መስሪያ ቤቱ የመዋቅር ማሻሻያ ቢያደርግ እንኳን፣ የጉምሩክ ፖሊስ አባላቱን ወደ ሌላ መደብ አዛውሮ የሚያሠራበት ወይም ለአዲሱ መዋቅር ብቁ እንዲሆኑ ሥልጠና ከመስጠት ውጪ “በመዋቅሩ ላካትታችሁ አልችልም” በማለት ማሰናበት አይችልም ሲል ፍርድ ቤቱ ወስኗል።
በመሆኑም የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ሠራተኞቹን ማሰናበቱን ከገለፀበት ጊዜ አንስቶ በነበሩበት የሥራ መደብና ደምወዝ እንዲመልሳቸው ትዕዛዝ በማስተላለፍ መዝገቡ ተዘግቶ ነበር።
ይህንን ውሳኔ የተቃወመው ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ፣ ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ይግባኝ ቢልም ይግባኝ ሰሚው የክርክሩን ውሳኔ በማፅናቱ ውሳኔውን ተግባራዊ እንዲያደርግ ይገደዳል።
የፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ አልተከበረልንም ያሉት ሠራተኞቹ ለአፈፃፀም “አቤት” በማለታቸው ትዕዛዙን አልፈፅምም ያለው የፍርድ ባለዕዳው የጉምሩክ ባለሥልጣን ሥራ አስኪያጁን ፖሊስ አፈላልጎ አስሮ፣ በማንኛውም የሥራ ሰዓት ፍርድ ቤት እንዲያቀርባቸው ታዟል።
ትዕዛዙ ከፍርድ ቤት ከወጣ 15 ቀናት ቢቆጠሩም የጉምሩክ ባለሥልጣን ዳይሬክተር እስካሁን ተይዘው አለመቅረባቸው ታውቋል።
በሌላ በኩል የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የጀመረውን አፈፃፀምና፣ የባለሥልጣኑን ሥራ አስኪያጅ ታስረው እንዲቀርቡ የሚያዘውን ትዕዛዝ፣ በሰበር ሰሚ ችሎት ማሳገዱን ገልጿል።
መስሪያ ቤቱ ለሁለት ጊዜ ያህል ቢወሰንበትም፣ የመጨረሻ ዕድሉን ለመሞከር ጉዳዩ በሰበር እንዲታይለትና እስከዚያው የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ትዕዛዙ እንዲታገድለት ባመለከተው መሠረት፣ ጥያቄው ተቀባይነት አግኝቶ ትዕዛዙ በሰበር ታግዷል። ጉዳዩን ለማየትም ለመስከረም 22 ቀን 2001 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል።



