በቫንኩቨር የሻማ ማብራት ሥነሥርዓት ተካሄደ
"የታረዱትንና በጥይት የተደበደቡት ኢትዮጵያዊያን ሰማእታት ናቸው ‘ነፍስ ይማር’ ወይንም RIP ሊባልለት የሚገባው በቁሙ ለሞተው አይሲስ ነው።" ዲያቆን መምህር አድማሱ ዘባን

Ethiopia Zare (ሰኞ ሚያዚያ 19 ቀን 2007 ዓ.ም. April 25, 2015)፦ ራሱን የእስላም መንግስት በማለት የሚጠራው እና ዘግናኝ ግድያዎችን በንጹሃን ዜጎች ላይ በመፈጸም ላይ በሚገኘው ቡድን እጅ ህይወታቸውን ላጡ ኢትዮጵያዊያኖችና በሳውዝ አፍሪካ የሚገኙ ወገኖች ላይ የሚፍጸመውን ሰብአዊነት የጎደለው አስከፊ ድርጊት በመቃዎም በቫንኩቨር (ካናዳ) ታላቅ የሻማ ማብራት ሥነሥርዓት ተካሄደ።
በዚሁ ቅዳሜ April 25/15 በኢትዮጵያ ኮሚኒቲ በብሪቲሽ ኮሎምቢያ ባስተባበረው ታላቅ የሻማ ማብራት ሥነሥርዓት ላይ በኮሚኒቲው ሊቀመንበር አቶ በረከት ከበደ ንግግር የተጀመረው ሥነሥርዓት ላይ በርካታ ኢትዮጵያዊያን የኤርትራ ሰዎችን ጨምሮ የኬንያና ሌሎች ሃገራት ዜጎች ተገኝተዋል።

በስፍራው የግብጽ ኮብቲክ ቤት ክርስቲያን መንፈሳዊ አባት በመገኘት ንግግር ያደረጉ ሲሆን በቫንኩቨር የምትገኘው ምስካየ ኅዙናን መድሃኒያልም እና ጼዴንያ ቅ.ማርያም ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ዲያቆን መምህር አድማሱ ዘባን በቡራኬ የጀመረውን ንግግር የኢትዮጵያንና የኢትዮጵያዊያንን እንግዳ ተቀባይነት ላይ መጠነኛ የታሪክ ትውስታ በማድረግ በሊቢያ የታረዱትንና በጥይት የተደበደቡት ኢትዮጵያዊያን ሰማእታት እንጂ ‘ነፍስ ይማር’ ወይንም RIP የሚባልላቸው አይደሉም ብሏል። በማያያዝም RIP ሊባልለት የሚገባው በቁሙ ለሞተው አይሲስ ብለው ራሳቸውን ለሚጠሩ ሰዎች ነው። በማለት ንግግሩን አጠናቋል።

የግሼን ደብረ ከርቤ ቤተ ክርስቲያን ዲያቆን ታምሩም ስሜታዊ በመሆን የጀመረውን ንግግር 'አንድ ሆነን' ለሃገራችን እንቁም በማለት ንግግር ያደረገ ሲሆን የጸጋ ቤተ ክርስቲያን ተወካይ አቶ ሀብታሙ በእንግሊዝና በአሜሪካዊያን ጋዜጠኞችና የርዳታ ድርጅት ሰራተኞች ላይ ከተፈጸመው የግፍ ግድያ የኢትዮጵያዊያኑ አሟሟት የሚለየውና እጅግ የሚያሳዝነው እናቴን እረዳለሁ፣ ወንድሜንና እህቶቼን ከችግር አላቅቃለሁ በማለት በበርሃ የሚከራተቱ ዜጎች ላይ እንዲህ አይነቱ ግድያ መፈጸሙ እጅግ እንደሚያሳዝን አጽንኦ ሰጥቶበታል።
በዝግጅቱ ላይ:-
"… የቀን ጨለማ ነው
ሰሞኑን በኢትዮጵያ የሆነው
ካለፉት ሁለት ሶስት ሳምንታት
ሲገረፉ፣ ሲቃጠሉ፣ ሲታርዱ ማየት
ይከበዳል ሰው ለሆነ ሰውነት… " የሚል ግጥም በመምህር ላሳብ አበበ የቀረበ ሲሆን ግጥሙ የተሰብሳቢውን ስሜት ነክቶ እንደነበርም ለማወቅ ተችሏል።
የኢትዮጵያዊያን ማህበረሰብ በብሪቲሽ ኮሎምበያ በሳውስ አፍሪካ ወገኖች ላይ የደረሰውንና እየደረሰ ያለውን ጭፍጨፋ በመቃወምና የሳውዝ አፍሪካ መንግስት ጉዳዩን ትኩረት ሰጠቶ እንዲመለከተው የሚጠይቅ ደብዳቤ በካናዳ ለሚገኘው ኤምባሲ ደብዳቤ ያስገባ ሲሆን ኢትዮጵያዊያኑ የሚደርስባቸው እንግልትና ግድያ በአስቸካይ እንዲቆምና ለጥቃቱ ሰለባዎች አስተማማኝ ጥበቃ እንዲደረግና ካሳ እንዲከፈላቸው ጠይቆ በአለማቀፍ ደረጃ የሚፈረም ፒቲሽን እንደበተነም ለማወቅ ተችሏል።
በተያያዘ በዚሁ በቫንኩቨር ከተማ በምትገኘው ምስካየ ኅዙናን መድሃኒያልም እና ጼዴንያ ቅ.ማርያም ቤተ ክርስቲያን አርብ April 24/2015 የጸሎት ሥነሥርዓት የተደረገ ሲሆን ትላንት እሁድ ደግሞ የቤተ ክርስቲያኗ አስተዳዳሪ መላከ ብርሃን ማእረግ በተገኙበት በግፍ ለተገደሉ ሰማእታት የፍታት ሥነሥርዓት ተደርጓል።



