Semahegn BelewEthiopia Zare (ማክሰኞ ሐምሌ 22 ቀን 2000 ዓ.ም. July 29, 2008)፦ ”በቸልተኝነት መኪና በማሽከርከር የሰው ሕይወት እንዲያልፍ አድርገሃል” ተብሎ ተከሶ ለነበረው ድምፃዊ ሰማኸኝ በለው የመከላከያ ምስክር ሆኖ የቀረበው ትራፊክ ፖሊስ ለሰማኸኝ በሐሰት መስክረሃል በሚል በዛሬው ችሎት ”ጥፋተኛ” መባሉን የኢትዮጵያ ዛሬ ድረ ገጽ ሪፖርተር ዘገበ።

 

ድምፃዊ ሰማኸኝ በለው የዛሬ ስድስት ዓመት ሐምሌ 7 ቀን 1994 ዓ.ም. ከሌሊቱ 10 ሰዓት ላይ አቶ ግሩም ተስፋዬ የተባለን የግጥምና ዜማ ደራሲ፤ በቸልተኝነት መኪና በማሽከርከር ባምቢስ ድልድይ ውስጥ በመክተት ሕይወቱ እንዲያልፍ አድርጓዋል ሲል ለመጀመሪያ ጊዜ ክስ የመሰረተው ትራፊክ ፖሊስ እሸቱ ሰዒድ በኋላ ላይ ሰማኸኝ በለው በመከላከያ ምስክርነት ለፍርድ ቤት ሲያቀርበው ሰማኸኝ ጥፋተኛ አይደለም ሲል መስክሩዋል በሚል ለቀረበበት ክስ በዛሬው ዕለት ጥፋተኛ ተባለ።

 

ድምፃዊ ሰማኸኝ በለው የዛሬ ስድስት ዓመት ሐምሌ 7 ቀን 1994 ዓ.ም. ከሌሊቱ 10 ሰዓት ላይ አቶ ግሩም ተስፋዬ የተባለ ግለሰብን በቸልተኝነት መኪና በማሽከርከር ባምቢስ ድልድይ ውስጥ በመክተት ነፍስ አጥፍተሃል ተብሎ ክስ ቀርቦበት በነበረ ጊዜ፤ ትራፊክ ፖሊስ እሸቱ ሰዒድን በምስክርነት ለፍርድ ቤቱ አቅርቦት ነበር። ፍርድ ቤቱ በመጨረሻ ሰማኸኝ በለውን ሦስት ሺህ ብር ቀጥቶ አሰናብቶታል።

 

ይኸው እሸቱ ሰዒድ የተባለው የትራፊክ ፖሊስ ለሰማኸኝ በለው በሰጠው የምስክርነት ቃል ተንተርሶ፤ ”መጀመሪያ ጥፋት ፈጽሟል ብለህ ክስ መሰረትክ፤ በኋላ ደግሞ ጥፋተኛ አይደለም ብለህ በሐሰት መስክረሃል” በሚል ባለፈው ዓመት ክስ ቀርቦበት ሲከራከር ቆይቷል።

 

ዛሬ በከፍተኛው ፍርድ ቤት 11ኛ ወንጀል ችሎት የትራፊክ ፖሊስ እሸቱ ሰዒድ በተከሰሰበት ክስ ጥፈተኛ ከተባለ በኋላ፣ ክሱ በአንድ ዓመት የሚያስቀጣ ቢሆንም፤ 24 ዓመት በሥራው ላይ የቆየ በመሆኑ፣ ባለፉት 24 ዓመታት ጥፋት ያልሠራ በመሆኑ እና የቤተሰብ ኃላፊ መሆኑን ግምት ውስጥ በማስገባት የአንድ ዓመት እስሩ ተቀይሮለት ሦስት ዓመት በገደብ እንዲቀጣ የቅጣት ውሳኔ ተላልፎበታል። ሦስት ዓመት በገደብ ማለት ለጊዜው የማይታሰር ሲሆን፣ በሦስት ዓመት ውስጥ ጥፋት ፈጽሞ ቢገኝ የአንድ ዓመት እስራቱ ተፈፃሚ ይሆናል።

 

ሰማኸኝ በለው በመጀመሪያ የተከሰሰው ሐምሌ 7 ቀን 1994 ዓ.ም. ከሌሊቱ 10 ሰዓት ላይ ግሩም ተስፋዬን በቸልተኝነት መኪና በማሽከርከር የሰው ነፍስ እንዲጠፋ አድርገሃል የሚል ሲሆን፣ ክሱ እየተካሄደ እያለ ዓቃቤ ሕግ ”ሌሎች ማስረጃዎች ስላለለኝ ክሴን ልቀይር” አለ። ፍርድ ቤቱ ዓቃቤ ሕግን ”ክስህን መቀየር አትችልም” ብሎት፤ ሰማኸኝ በለውን ሦስት ሺህ ብር ቀጥቶ አሰናበተው።

 

ዓቃቤ ሕግ ”ማስረጃዎችን በማግኘቴ ክሴን ላሻሽል ስል እንቢ ተባልኩ። ሰማኸኝ በለው ግሩም ተስፋዬን የገደለው ሆን ብሎ አስቦና አቅዶ የመኪናው መሪ ላይ አስደግፎ ባንቢስ ድልድይ ውስጥ ገፍትሮ በመክተት ነው። ለዚህ ደግሞ ማስረጃ አለኝ” በማለት ነበር ይግባኝ የጠየቀው።

 

በዚህ ዓቃቤ ሕግ በጠየቀው ይግባኝ ሰማኸኝ ሁለቴ ፍርድ ቤት እንዲቀርብ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ያስተላለፈ ቢሆንም፤ በሁለቱም ቀጠሮዎች ላይ አልተገኘም። ካለፉት ቀጠሮዎች የመጨረሻው ቀጠሮ ሰኔ 27 ቀን 2000 ዓ.ም. ነበር።

 

ቀጣዩ የይግባኝ ቀጠሮ ሐምሌ 30 ቀን 2000 ዓ.ም. መሆኑን የተረዳን ሲሆን፣ ሰማኸኝ በለው ግን ከመጋቢት 2000 ዓ.ም. በፊት ከሀገር ቤት እንደወጣና አሜሪካን ሀገር እንዳለ ለመረዳት ችለናል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ