ሰማኸኝ በለው በነፍስ ማጥፋት ክሱ ይግባኝ ተጠየቀበት
Ethiopia Zare (ኀሙስ መጋቢት 11 ቀን 2000 ዓ.ም. March 20,2008)፦ ድምፃዊ ሰማኸኝ በለው የዛሬ ስድስት ዓመት ሐምሌ 7 ቀን 1994 ዓ.ም. ከለሊቱ 10 ሰዓት ላይ አቶ ግሩም ተስፋዬ የተባለ ግለሰብን በቸልተኝነት በመኪና በመግጨት ባምቢስ ድልድይ ውስጥ በመክተት ነፍስ አጥፍተሃል ተብሎ ክስ ቀርቦበት ፍርድ ቤቱ ሦስት ሺህ ብር ቀጥቶ አሰናብቶት ነበር።
የፌዴራሉ ዓቃቤ ሕግ ፍርድ ቤቱ የሰጠውን ውሳኔ "ፍትሃዊ ያልሆነና ማስረጃዎቹን ያላገናዘበ በመሆኑ በወንጀሉ ጥፋተኛ ተብሎ መቀጣት አለበት" ሲል ይግባኝ መጠየቁን ለማወቅ ችለናል።
"ድምፃዊ ሰማኸኝ በለው፤ ግሩም ተስፋዬን በቸልተኝነት በመኪና ገጭቶ መግደሉ በበቂ ሁኔታ በማስረጃ ተረጋግጦበት እያለ ፍርድ ቤቱ እጅግ በቀለለ ቅጣት ማሰናበቱ አግባብ አይደለም" ሲል ዓቃቤ ሕግ ለፍርድ ቤት ባቀረበው የይግባኝ ጥያቄ ላይ ማስፈሩን ከአዲስ አበባ ለኢትዮጵያ ዛሬ ድረ-ገጽ የደረሰው ዘገባ ያስረዳል።
በዚሁ ይግባኝ ላይ ዓቃቤ ሕግ "ድምፃዊው ድርጊቱን ስለመፈፀሙ ማረጋገጫ የሚሆኑ ማስረጃዎች የቀረቡ በመሆናቸው ጥፋተኛ ተብሎ ሊቀጣ ይገባል" ሲል ጠይቋል።



