Ethiopia in the year 2011 Ethiopian calendar

የኢትዮጵያ ከራሞት በ2011 ዓ.ም. - ክፍል 1

በኢትዮጵያ ዛሬ ዝግጅት ክፍል የተጠናከር ዘገባ

እንደ መግቢያ

ኢትዮጵያውያን ከዚህ በኋላ አሮጌው የሚሉትን የ2011 ዓ.ም. ጉዞ አጠቃለው አዲሱን ዓመት 2012 ተቀብለዋል።

2011 የበጀት ዓመት ኢትዮጵያ ብዙ ፈተናዎችን ያስተናገደችበት ነበር ማለት ይቻላል። የበረቱ ፈተናዎችን ያስተናገደች ቢሆንም ግን ተስፋ የሚሰጡ ታሪካዊ የሚባሉ ክንውኖችንም ያስተናገደችበት ነበር። በማኅበራዊ፣ በፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ብዙ ችግሮች አጋጥመዋታል። ብዙ ተስፋ ሰጪ ክንውኖችን መመልከት የቻለችበት ዓመትም እንደነበር።

በርካታ ክንውኖችን መመልከት የተቻለበት ስለመሆኑ ብዙ ማሳያ የሚሆኑ መረጃዎች ማቅረብ የሚቻልበት ዓመት ነው። በዶ/ር ዓብይ የሚመራው የለውጥ ኃይል ያስገኘውን ዴሞክራሲያዊ ነፃነት ባለመቀበል ወይም በመጠራጠር የሚናፈሱ ወሬዎች ግን የለውጡን ሒደት ሲገዳደሩ እንደነበር መመልከት ተችሏል።

በጥቅል ሲታይ ግን፤ ተስፋ የሚሰጡ መልካም ክንውኖች የመታየታቸውን ያሕል፤ ሥጋት የሚጭሩ፣ ብዥታ ውስጥ የከተቱ ተግባራትንም እየተመለከትን 2011ን አጠቃለናል።

ከፖለቲካ ጉዳዮች አንፃር 2011 የበረከቱ ክስተቶችን አስተናግደናል። ያለፈው ዓመት የመጀመርያ ወር መስከረም 1 ቀን 2011 ዓ.ም. ከተከሰተው እንግዳ ክስተት እንጀምር።

የኢትዮ-ኤርትራ ድንበር ተከፈተ - ተዘጋ

2011 ኢትዮጵያውያን አዲሱን ዓመት በመቀበል ብቻ የሚያስታውሱት አልነበረም። መስከረም 1 ቀን 2011 ዓ.ም. በተለየ እንዲታወስ የሚያደርገው ከ20 ዓመታት በላይ የተዘጋው የኢትዮ-ኤርትራ ድንበር የሁለቱ አገር መሪዎች በዛላምበሳ ድንበር ተገኝተው ማስከፈታቸው ነበር።

2011 እና የኢትዮ-ኤርትራን ወቅታዊ ግንኙነት ወደ አዲስ ምዕራፍ መሸጋገሩን ያሳየ መሆኑን ያሕል፤ እስካሁን ሁለቱ አገሮች ይተሳሰሩበታልና ይገዙበታል የተባለው የንግድ ግንኙነት ሰነድ ሥራ ላይ አልዋለም። እንደውም በድንበሩ መከፈት የተጀመረው የድንበር አካባቢ ንግድ መነቃቃት የፈጠረ ቢሆንም፤ ድንበሩ በድጋሚ ተዘግቷል። ለዚህ የተሠጠው ምክንያት ደግሞ የንግድ ልውውጡን ሕጋዊ በሆነ መንገድ ለማስኬድ ታስቦ እንደሆነም ተገልጿል። በነገራችን ላይ መስከረም 1 ቀን 1945 ዓ.ም. ኤርትራ ከእናት አገርዋ የተቀላቀለችበት ነበር።

የኦነግ ወደ አገር ውስጥ መግባት

በዓመቱ የመጀመርያ ወር በሆነው መስከረም 5 ቀን 2011 ዓ.ም. በአገሪቱ የፖለቲካ ታሪክ ሊጠቀስ የሚችለው ክንውን ደግሞ፤ በዳውድ ኢብሳ የሚመራው ኦነግ ወደ አገር ቤት መግባቱ ነው።

ዳውድ ኢብሳንና ሌሎች አመራሮችን ለመቀበል በመስቀል አደባባይ የወጣው ሕዝብ ቁጥር ከፍተኛ ነበር። ኦነግን ለመቀበል አስፓልትና ግድግዳ ኦነግን በሚገልጹ ቀለማት መቀባት በአገሪቱ የፖለቲካ ትግል ውስጥ እንግዳ የሆነ ተግባር ሳር ቅጠሉን በቀለም ለመቀባት የተደረገው እንቅስቃሴ አግራሞት ከማጫሩ ባለፈ ግጭትም የፈጠረ እንደነበር የሚታወስ ነው። በተለይ አስፓልት፣ ግድግዳ፣ የተቋማት በርና መስኮትን መቀባት አግባብ አለመሆኑን የገለፁ ወጣቶች፤ ቀለም ሲቀቡ ከነበሩ የኦነግ ደጋፊ ወጣቶች ጋር ተጋጭተዋል። ለሕይወት መጥፋት መንስዔም ነበር ማለት ይቻላል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድን ከአስመራ ተሳፍረው አዲስ አበባ የገባው በዳውድ ኢብሳ የሚመራው ኦነግ ከመግባቱ በፊትና በኋላም በኦነግ የትግል ታሪክ ውስጥ በከፍተኛ አመራር ደረጃ የነበሩ አባላትም አዲስ አበባ ገብተዋል። የኢትዮጵያን ምድር ለመርገጥ እርግጠኛ ያልነበሩ የኦነግ አመራሮችና ሌሎችም የፖለቲካ አመራሮች ወደ ኢትዮጵያ ገብተው ከሕዝብ ጋር መወያየት የጀመሩት፣ በየሚዲያው ተጋብዘው አለመካተታቸውና እምነታቸውን በሰፊው መግለጽ የቻሉበት ዓመት 2011 ዓ.ም. ነው ማለት ይቻላል።

ኦነግና ኦሕዴድ (ኦዴፓ - አዲሱ ስሙ)

በሰላማዊ ትግል በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ለመንቀሳቀስ በገባው በኦነግና በኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) መካከል ያለመግባባት ስለመፈጠሩም የተሰማው በዚህ ዓመት ነው። “ኦነግ ትጥቅ አልፈታም” አለ ተብሎ መነገሩ በተለይም አቶ ዳውድ ኢብሳ “ትጥቅ ፈቺው ማነው? አስፈቺውስ?” ብለው የመናገራቸው ነገር ብዙ ሲያነጋግር ነበር። ይህ አባባል ትክክል ያለመሆኑንና በአንድ አገር ውስጥ ትጥቅ በሕጋዊ መንገድ መያዝ ያለበት መንግሥት ወይም የመንግሥት ታጣቂ ኃይል ብቻ በመሆኑ፤ የኦነግ አመራሮች አገላለጽ ብዙ ትችት አስተናግዷል። በዚሁ ጉዳይ ላይ “አቶ ዳውድ ኢብሳ ትጥቅ አስፈቺው ማነው ብለዋል” ተብለው ለቀረበላቸው ጥያቄ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲመልሱ፤ “ይህ የምላስ ወለምታ ይመስለኛል” በማለት መግለጻቸውም ይታወሳል። እንዲህ ያሉ ነገሮች ብዙ አወዛግቦ በመጨረሻ በኦነግ ስም የታጠቀ ሠራዊት መኖር የለበትም ተብሎ አባገዳዎችና ሌሎች ሸምጋዮች ገብተው ኦነግ ያሉኝን ታጣቂዎች ለአባገዳዎች አስረክባለሁ ማለቱ ይታወሳል። በመጨረሻም ከአስር ሺህ በላይ አሉኝ ካላቸው ታጣቂዎች ስምንት መቶዎቹን ያህል አስረክቦ፤ ከነኝህ ውጭ ምንም ዐይነት የታጠቀ ኃይል የለኝም ብሎ በማሳወቅ ጉዳዩ በሰላማዊ መንገድ መቋጨቱ የተገለጸበት ዓመት ነው።

አስደንጋጩ ክስተት

በ2011 በመጀመርያዎቹ ወራት ከተሰሙ አስደንጋጭ ወሬዎች አንዱ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የሚመራውን ሥርዓት ለመጣል ተፈጸመ የተባለው ያልተሳካ የ“መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ” ነው። ይህም የሆነው ከጥቅማ ጥቅሞች ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች አሉን ያሉ የታጠቁ ወታደሮች ጠቅላይ ሚኒስትሩን ማነጋገር እንፈልጋለን ብለው ቤተ መንግሥት መዝለቃቸው ነበር።

እነዚህ ታጣቂዎች ለመንግሥት ግልበጣ መምጣታቸው ግን የታወቀው ወይም ሐሳባቸው ግልበጣ መሆኑ የተሰማው ዘግይቶ ቢሆንም፤ በወቅቱ ታጣቂዎቹን ዘዴ ትጥቅ እንዲፈቱ ተደርጎ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ፑሽአፕ ሠርተውና ራት በልተው እንዲሸኙ በማድረግ ለማክሸፍ ተችሏል። ነገር ግን ጉዳዩ ተጣርቶ በዚህ ያልተገባ ተግባር ተሳታፊ ናቸው የተባሉ ወታደሮች ፍርድ ቤት ቀርበው ተፈርዶባቸዋል። በኋላም በምሕረት የተለቀቁበት ዓመት ነው።

በዚህ ያልተገባ ተግባር የተበሳጩት የቀድሞ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል ሰዓረ መኮንን ድርጊቱን “ጋጠወጥ ተግባር” ነበር ያሉት። ዶ/ር ዓብይም ነገሩን በፑሽአፕ ያሳለፉኩት “እርር ድብን” ብዬ ነው ማለታቸውም አይዘነጋም።

እኝህ በቤተ መንግሥት ተገኝተው የጥቅማ ጥቅም ጥያቄ ማቅረብ ፈልገነው ብለው የመጡትና በኋላ ላይ ዓላማቸው ሌላ መሆኑ ተረጋግጦ ወታደራዊ ፍ/ቤት ቀርበው ፍርድ የተላለፈባቸውና በኋላም በምሕረት ተለቀዋል የተባሉት ወታደሮች ስም ከወራት በኋላ የተነሣበት አጋጣሚ ፈጥሯል። ይህም በኢትዮጵያውያን ዘንድ መሪር ኀዘን የፈጠረው የአማራ ክልላዊ መንግሥት አመራሮችና በፌዴራል ደረጃ በኤታማዦር ሹሙና በቀድሞ የሎጂስቲክ ኃላፊ ጀኔራል ላይ ከተፈጸመው ግድያና በአማራ ክልል በተፈጸመውና መንግሥት “መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ” ነበር ካለው ጋር የተያዘ ነው። ስማቸው ድጋሚ የተነሣውም አንዳንዶቹ በምሕረት የተለቀቁ ወታደሮች እንደነበሩ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መጥቀሳቸው ነው።

የሴት ሹመኞችቭ መንገሥ

የአገሪቱ ሌላው አብይ ፖለቲካዊ ክንውን ከኢትዮጵያ ሃያ ሚኒስትር መሥሪያ ቤቶች ግማሽ ያህሉ ሴቶች ሆነው መሾማቸው ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በዚህ ሹመታቸው የመጀመርያ ሴት የመከላከያ ሚኒስትር ሾመዋል፤ ምንም እንኳን ከወራት በኋላ በወንድ ቢተኩም። በአገሪቱ ቁልፍ ከሚባሉ ተቋማትን ሴቶ እንዲመሩ የሾሙት ጠ/ሚኒስትሩ፤ በአንዳንድ ሹመቶች ለመጀመርያ ጊዜ ሴቶች በኃላፊነት እንዲቀመጡ አድርገዋል።

እንደ ምሳሌ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፐሬዝዳንት ወ/ሮ መአዛ አሸናፊና የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ በመሆን የተሾሙት ወ/ሮ ብርቱካን ሚደቅሳ የሚጠቀሱ ናቸው። የአገሪቱ ርዕሰ ብሔር በመሆን የተሰየሙት ወ/ሮ ሣህለወርቅ ዘውዴ የመጀመሪያዋ ሴት ፕሬዝዳንት የሆኑበት ዓመት ነው። በዓመቱ ለየት ካሉ ሹመቶች መካከል አሁን ላለው ለውጥ በመሪነት የሚጠቀሱት አቶ ለማ መገርሳ መከላከያ ሚኒስትር ሆነው መሾማቸው፤ በተመሳሳይ መንገድ አሁን ላለው ለውጥ ያበረከቱት አስተዋጽኦ ያላቸው አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፣ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየውን ተክተው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መሆናቸው በዚህ ዓመት ከተደረጉት የአመራር ለውጦች በቀዳሚነት የሚጠቀሱ ናቸው።

ከአዳዲስ ሹመቶች ጋር በተያያዘ የለውጥ አመራሩ እንደ ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ያሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ የሆነ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር አድርጐ መሰየሙ የሚጠቀስ ነው።

የምርጫ ሕግጋትና አከራካሪው ነጥብ

የዴሞክራሲ ምኅዳሩን ለማስፈን ከተደረጉ ማሻሻያዎች መካከል የምርጫ ሕግጋትን ማሻሻል ነው። በማሻሻሉ ሒደት የተቃዋሚ ፓርቲዎች እንዲሳተፉ ተደርጓል።

ከዚህ ቀደም አሳሪ ናቸው የተባሉ ምርጫን የተመለከቱ ሕግጋቶች ውስጥ የነበሩ አንቀጾች እንዲለወጡ ተደርጓል። በዚህ ሕጉን የማሻሻያ ሥራ በብዛት ሁሉንም የፖለቲካ ፓርቲዎች ያስማማ ረቂቅ እንዲዘጋጅ አስችሏል። በፓርላማ እንዲፀድቅ የተደረገበትም ዓመት ነው። ይሁንና ጥቂት የማይባሉ ፓርቲዎች ረቂቁ የፀደቀው ከእኛ አመለካከት ውጭ ነው በማለት ተቃውሞዋቸውን አሰምተዋል። በተለይ “አንድ የፖለቲካ ፓርቲ ሕጋዊ እውቅና ለማግኘትና በምርጫ ቦርድ ለመመዝገብ አሥር ሺሕ ፊርማ ማሰባሰብ አለበት” በሚል የተደነገገውን አዲሱን ሕግ አልተቀበሉትም። በየደረጃው ፓርቲዎች ማቅረብ አለባቸው የተባለው የድጋፍ ፊርማ ቁጥር በዛ በሚል የተከራከሩበት ነበር። በዚህ ቁጥር ላይ እነ ኦነግ፣ ኢዜማና የመሳሰሉ ፓርቲዎች ይህንን ድጋፍ ለማቅረብ ችግር የለብም ሲሉ ተደምጠዋል። ሌሎቹ ግን አሁን አገሪቷ ካለችበት አለመረጋጋት አንፃር ይህንን ማድረግ ይከብደናል ብለዋል።

የጤና ባለሙያዎች

በዚህ ዓመት ሌላው ክስተት በተለይ የጤና ባለሙያዎች ያቀረቡት የጥቅማ ጥቅምና ከዚሁ ጋር ተያይዞ ሥራ ለማቆም የተደረገው ሙከራ ውጥረት ፈጥሮ ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩም እነዚህን ባለሙያዎች ለማነጋገር የተገደዱበትና አንዳንድ ማስተካከያዎች የተደረጉበት ዓመት ነው።

ተፈናቃዮች

በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የነበረው የተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ የተደረጉ ጥረቶች መንግሥትን የፈተነ ጉዳይ ሆኖ አልፏል። መጨረሻ ላይም አብዛኛውን ተፈናቃይ መመለስ መቻሉ ተደምጧል። ከመንግሥት መግለጫ መረዳት እንደተቻለውም አብዛኛው ተፈናቃይ ወደነበረበት ቦታ የመመለሱ ሥራ መሳካቱን ነው።

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!