images/doc/images/news/2019/191022-pm-abiy-ahmed-winner-of-nobel-peace-prize.jpg

አቶ ሽመልስ አብዲሳ (በግራ)፣ ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ (መሐል)፣ አቶ ለማ መገርሳ (በቀኝ)

“ዳውን ዳውን ዐቢይ! ዳውን ዳውን ቲም ለማ!” የአምቦ ቄሮዎች

ኢዛ (ሐሙስ ጥቅምት ፳ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. October 31, 2019)፦ በአምቦ ከተማ “የሰላም ኮንፈረንስ” ላይ ለመሳተፍ ወደ ከተማይቱ ያቀኑት ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ፤ በውይይቱ እንዳንሳተፍ ተከልክለናል ባሉ የከተማይቱ ቄሮች ከፍተኛ ተቃውሞ ገጠማቸው። ከጠቅላይ ሚንስትሩ ጋር የመከላከያ ሚንስትሩ አቶ ለማ መገርሳና የኦሮሚያ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ነበሩ።

ከዛሬ ጠዋት ጀምሮ ውይይቱ የተካሔደው በከተማይቱ በሚገኘው የአበበች መታፈሪያ ሆቴል ሲሆን፤ በውይይቱ ላይ የተሳተፉት ከአምቦ፣ ከደቡብ ምዕራብ ሸዋ፣ ከምዕራብ ሸዋ፣ ከቡራዩ፣ ከወሊና ከሆለታ ከተሞች የተውጣጡ የሕብረተሰቡ ክፍሎች ተወካዮች መኾናቸው ታውቋል።

የቄሮዎች የተቃውሞ ምክንያት ነው የተባለው፤ በዚህ የሰላም ኮንፈረንስ ላይ ቄሮዎች እንዳይሳተፉ በመደረጋቸው እንደኾነ ታውቋል። ለኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄ ሲታገል የነበረው ቄሮ እንጂ፤ በስብሰባው ላይ የተሳተፉት ወገኖች አለመኾናቸውን ተቃውሞውን ሲያሰሙ የነበሩት ቄሮዎች ገለጸዋል።

በከተማይቱ አውራ ጉዳናዎች ላይ ቄሮዎቹ ሲያሰሟቸው ከነበሩት መፈክሮች ውስጥ፤ “ዳውን ዳውን ዐቢይ!”፣ “ዳውን ዳውን ቲም ለማ!”፣ “ዐቢይ እኛን ለማስተዳደር አይችልም!”፣ “የመጣው ሊያታልለን ነው!”፣ … የሚሉ ይገኙባቸዋል።

የከተማይቱ አውራ ጎዳናዎች በከፍተኛ ሁኔታ ይጠበቁ የነበረ ሲሆን፣ ቀይ መለዮ ለባሽ ጠብመንጃ ያነገቡ ወታደሮች የፀጥታ ጥበቃ ሲያደርጉ እንደነበር ለኢትዮጵያ ዛሬ የደረሰው ዘገባ ያስረዳል። ይህንንም ተከትሎ ውይይቱ ሲጠናቀቅ ጠቅላይ ሚንስትሩ በሔሊኮፕተር ከተማይቱን ለቅቀው እንደወጡ ለማወቅ ተችሏል።

ባለፈው ሳምንት ረቡዕ (ጥቅምት 12 ቀን 2012 ዓ.ም.) አክቲቪስት ጃዋር መሐመድ “ተከብቤአለሁ” በማለት በፌስቡክ ያሠራጨውን መልእክት ተከትሎ፤ ለሁለት ቀናት (በአንዳንድ አካባቢዎች ለሦስት ቀናት) ኹከትና ግጭት ካስተናገዱት ከተሞች ውስጥ አምቦ አንዷ እንደነበረች ይታወቃል።

በአገሪቱ የተለያዩ የኦሮሚያ ከተሞች፣ እንዲሁም ድሬዳዋና ሐረር በተከሰተው በዚሁ ኹከት፤ የ78 ንጹሐን ዜጎች ሕይወት የተቀጠፈ ሲሆን፣ በርካታ ሰዎች የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል። በኹከቱ ከዚህም ሌላ ለጊዜው በውል ያልታወቀ ንብረት ወድሟል፣ ዜጎች ከቦታ ቦታ የመዘዋወር መብታቸውን ተነፍገዋል፣ የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ታይተዋል፣ የሃይማኖት ተቋማት ውድመትና የሃይማኖት አባቶች ጥቃት ደርሶባቸዋል። ይህንንም ተከትሎ በአገሪቱ የሚገኙ የሃይማኖት ተቋማት፣ የሰብዓዊ መብት ተቋማት፣ ታዋቂ ሰዎች፣ የፖለቲካ ድርጅቶች “ጥፋተኞች ለሕግ ይቅረቡ!”፣ “የሕግ የበላይነት ይከበር!” የሚሉ መግለጫዎችና አስተያየቶችን በስፋት ሲያቀርቡ ተደምጠዋል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ