ኦቦ ለማ መገርሳ በለጸጉ

ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድና ኦቦ ለማ መገርሳ
ኦቦ ለማ ልዩነታቸውን አጥብበው ለመሥራት መስማማታቸው ተሰማ
ኢዛ (ሰኞ ታኅሣሥ ፲፫ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. December 23, 2019)፦ በመደመር ፍልስፍናና በፓርቲዎቹ ውሕደት ላይ ያላቸውን ልዩነት በመግለጽና ይህንንም በይፋ ተቃውመው የነበሩት የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ለማ መገርሳ፤ ልዩነታቸውን በማጥበብ የሕዝቡን ትግል ወደቀጣይ ምዕራፍ ለማሸጋገር መስማማታቸው ተሰማ።
አቶ ለማ በመደመር ፍልስፍናና በፓርቲዎቹ ውሕደት (ሦስቱ የኢሕአዴግ እኅት ድርጅቶችና አምስቱ አጋር ድርጅቶች ተዋሕደው ብልጽግና ፓርቲ መባላቸው) ዙሪያ ያላቸውን ልዩነት ከሰላ ሒስ ጋራ ከገለጹ በኋላ፤ የያዙትን አቋም ፓርቲው ውስጥ ኾነው እንደሚታገሉበት አስታውቀው እንደነበር አይዘነጋም።
ዛሬ ይፋ በኾነ መረጃ ግን፤ ይዘውት የነበረውን ልዩነት ለማጥበብ ስለመስማማታቸው ተገልጿል።
ይህንን ጉዳይ በተመለከተ መረጃውን ይፋ ያደረገው ኦቢኤን (OBN)፤ አቶ ለማ በፓርቲዎቹ ውሕደትና በመደመር ፍልስፍና ላይ ያላቸውን ልዩነት በኦሮሞ ባሕል መሠረት ለማጥበብ ስምምነት ላይ ስለመደረሱ ዘገባው ያስረዳል።
OBN፣ “በኦሮሞ ባሕል መሠረት ስምምነት ከተደረገ በኋላ ልዩነታቸውን አጥብበው፤ ከዚህ በኋላ በጥንካራ አንድነት በጋራ በመሥራት የሕዝቡን ድል ወደ አዲስ ምዕራፍ ለማሸጋገር ከስምምነት ተደርሷል።” ይላል።
ስምምነቱ የተደረሰው የቀድሞ የኦዴፓ ሥራ አስፈፃሚዎችና ነባር አመራሮች በጋራ ባደረጉት ውይይት መኾኑ ተጠቅሷል።
ፓርቲው የዴሞክራሲ ሥርዓትና በኦሮሞ ባሕል መሠረት ውስጣዊ ችግሮቹንና የሕዝቡን ጥያቄ ለመመለስ ጠንክሮ እንደሚሠራ የሚያትተው ይኸው ዘገባ፤ በፖለቲካ ሒደት ልዩነቶች መኖራቸው የተለመደ መኾኑን ጠቅሷል።
በዚህ ስምምነት ዙሪያ ዝርዝር መረጃ ባይሠጥም፤ የኢሕአዴግ ድረገጽ ላይ “ሁለቱ የለውጥ መሪዎች የተጀመረውን አገራዊ ለውጥ አብረው ያስቀጥላሉ” በሚል ርዕስ ባቀረበው ሰፊ ጽሑፍ፤ የተፈጠርው ልዩነት ለውጡ ዘለቄታ እንዲኖረው እንዴት እንምራው የሚል የተወሰነ የአካሔድ ልዩነት እንጂ፤ በሚወራው ደረጃ ትልቅ ልዩነት እንዳልነበረ ይገልጻል።
በጽሑፉ መጨረሻ ላይም፤ “በመኾኑም አሁንም የሐሳብ ልዩነታቸው ላይ በሠለጠነ አካሔድ ቁጭ ብለው ከተከራከሩበት በኋላ፤ የሐሳብ ልዩነታቸውን ፈትተው ለውጡን አብረው ለመሥራት ተስማምተዋል” ይላል። (ኢዛ)