በህዳሴ ግድብ ላይ በዋሽንግተን የተደረገው ውይይት መቋጫ እያነጋገረ ነው
የህዳሴ ግድብ
ከሁለት ሳምንት በኋላ የመጨረሻ ስምምነት ይጠበቃል
ኢዛ (ሐሙስ ጥር ፯ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. January 16, 2020)፦ ባለፉት ሁለትና ሦስት ወራት በተከታታይ በተደረጉ ውይይቶች ላይ ስምምነት ሳይደርሱ የቀሩት ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ በህዳሴ ግድብ ላይ ለሁለተኛ ጊዜ በዋሽንግተን ያካሔዱትን ውይይት ቢያጠናቅቁም የደረሱበት ድምዳሜ ግን ብዥታ ፈጥሯል።
ከአንድ ሳምንት በፊት አዲስ አበባ ላይ በተደረገ ውይይት ሳይስማሙ የቀሩት የተወያይ አገሮቹ ተወካዮች፤ ከቀናት በኋላ በዋሽንግተን ዲሲ የውኃ ሀብት ሚኒስትሮችና የልዑካን ቡድኖቻቸው በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ከጥር 4 - 6 ቀን 2012 ዓ.ም. ሲያካሒዱት የነበረው ውይይት ከቀደሙት ውይይቶች በተለየ ምን ተገኘ የሚለው ጉዳይ በዝርዝር አልተገለጸም። ኾኖም በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ እንደገለጸው ውይይቱ በመልካም ሁኔታ መጠናቀቁን ነው።
ውይይቱ የተካሔደው የአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስትር ስቲቨን ሙንሺንና የዓለም ባንክ ፕሬዚዳንት ዴቪድ ማልፓስ በተገኙበት እንደኾነ የሚጠቁመው ይኸው የኤምባሲው መረጃ፤ ውይይቱ ከዚህ ቀደም ተቋርጦ የነበረውን የቴክኒክ ውይይት በማስቀጠል በሦስቱ አገራት ዋና ከተሞች በአራት ዙር በውኃ ሀብት ሚኒስትሮች ሰብሰቢነት እንዲሁም በዋሽንግተን ዲሲ በሦስት ዙር በተካሔዱት ውይይቶች ዙሪያ ሪፖርት ቀርቦ የስትራቴጂካዊ ውይይት በማድረግ በመግባባት ስለመጠናቀቁ ያትታል።
ከዚህም በመነሳት በእስካሁኖቹ የድርድር ሒደቶች የነበሩትን ልዩነቶች በጋራ ተጠቃሚነት መንፈስ በመፍታት ወደ መጨረሻ ስምምነት ለመድረስ በሚያስችሉ ነጥቦች ላይ የሐሳብ ልውውጥ ስለመደረጉና ጥር 19 እና 20 ቀን 2012 በዋሽንግተን ዲሲ በመገናኘት የመጨረሻ ስምምነት ላይ ለመድረስ መግባባት ላይ ደርሰዋል ተብሏል። በመካከል ባለው ጊዜ ወቅት የሦስቱም አገራት የሕግ ባለሙያዎች የተወከሉበት ቡድን በሕግ ማዕቀፎቹ ላይ የጋራ ምክክር የሚያካሒድ ይሆናል ተብሏል።
በሰሞኑ የኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን የውጭ ጉዳይና የውኃ ሚኒስትሮች ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ዳግም የተወያዩ ሲሆን፤ ትራንፕ ከሦስቱ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር የመከሩት ለሁለተኛ ጊዜ ነው።
ትራንፕ የሦስቱን አገራት መሪዎች ያወያዩት የሦስቱ አገራት ልዑካን በዋሽንግተን ዲሲ እያደረጉ ከነበረው የውይይት ፕሮግራም ጐን ለጐን ሲሆን፤ ተወያዮቹን ለሁለተኛ ጊዜ ያወያዩበት ዝርዝር ጉዳይ በግልጽ አልተቀመጠም።
በተከታይ ውይይቶች ስምምነት ሳይደረስበት የቆየው የሦስቱ አገራት የጋራ የውይይት መድረክ ላለመስማማት እንደ ምክንያት የሚቀርበው፤ በግድቡ ውኃ አሞላል ላይ ግብጽ አዳዲስ ሐሳብ ይዛ ከመምጣቷ ጋር ይያያዛል። በቀጣይ ለሦስተኛ ጊዜ በዋሽንግተን የመጨረሻ የተባለው ውይይት እንዴት ይስማሙበታል? የሚለው ጥያቄ አሁንም አነጋጋሪ ቢሆንም፤ ከሰሞኑ ግን የግድቡ ውኃ አሞላል ጉዳይ ቀድሞም ቢሆን በመወያያ አጀንዳ መኾኑ ትክክል አልነበረም የሚል የኢትዮጵያ ምሁራን አንደበት እየተሰማ ነው። (ኢዛ)



