ድሬ ዳዋ ዩኒቨርሲቲ የተቋረጠውን ትምህርት መጀመሩን ገለጸ

ድሬ ዳዋ ዩኒቨርሲቲ
ትምህርት ያቋረጡት ተማሪዎች በሙሉ ወደ ዩኒቨርሲቲው አልተመለሱም
ኢዛ (ኀሙስ ጥር ፳፩ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. January 30, 2020)፦ የመማር ማስተማር ሒደቱን አቋርጦ የቆየው የድሬ ዳዋ ዩኒቨርሲቲ በከፊል የመማር ማስተማር ተግባሩን ስለመጀመሩ ገለጸ። ትምህርት ያቋረጡት ተማሪዎች በሙሉ ወደ ዩኒቨርሲቲው አልተመለሱም።
በተለያዩ ግጭቶችና ሰላም መደፍረስ ምክንያት የዩኒቨርሲቲው ሴኔት የመማር ማስተማሩን ተግባር እንዲቋረጥ ተደርጎ ነበር።
ዩኒቨርሲቲው በፌስቡክ ገጹ ላይ እንደገለጸው ደግሞ፤ የመማር ማስተማር ሒደቱን ከጥር 18 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ መቀጠሉን አስታውቋል።
ተማሪዎች በተደረገላቸው ጥሪ መሠረት ከጥር 14 ቀን ጀምሮ ወደ ዩኒቨርሲቲው እንደገቡና ከጥር 18 ቀን ጀምሮ በትምህርት ገበታቸው ላይ መገኘት መጀመራቸውንም ዩኒቨርሲቲው በፌስቡክ ገጹ ገልጿል። ቀሪ ተማሪዎችም በተቻለ ፍጥነት በትምህርት ገበታችው እንዲገኙ ጠርቷል።
ከትናንት በስቲያ (ጥር 19 ቀን 2012 ዓ.ም.) የዩኒቨርሲቲው የሰላም ኮንፈረንስ ካደረገ በኋላ ትምህርት ሊጀመር ችሏል። በትናንትናው ዕለትም ወደ ዩኒቨርሲቲው የተመለሱ ተማሪዎች በተሻለ ሁኔታ ትምርታቸውን ሲከታተሉ እንደዋሉ ገልጿል።
ዩኒቨርሲቲው ባለፈው ሳምንት የዩኒቨርሲቲውን ምክትል ፕሬዝዳንት ማባረሩ የሚታወስ ሲሆን፣ ለዩኒቨርሲቲው አለመረጋጋት ምክንያት ናቸው ባላቸው ተማሪዎች ላይ የተለያዩ አስተዳደራዊ እርምጃዎችን ጨምሮ እስከእገዳ የደረሰ ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል። (ኢዛ)