የሐረር ከተማ መውጫና መግቢያ በቡድን በተደራጁ ወጣቶች ተዘግቶ ዋለ

ሐረር ከተማ
የድሬ ዳዋ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ወደ ከተማዋ እንዳይገቡ ደንገጎ ላይ መንገድ ተዘጋባቸው
ኢዛ (ኀሙስ ጥር ፳፩ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. January 30, 2020)፦ በዛሬው ዕለት በሐረር ከተማና አካባቢው ሰዎች ከከተማ እንዳይወጡና እንዳይገቡ መንገድ የተዘጋባቸው ሲሆን፤ ወደ ድሬ ዳዋ ይጓዙ የነበሩ የድሬ ዳዋ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና ሌሎች ተጓዦች ከወደ አዲስ አበባ ሊገቡ ሲሉ ደንገጎ በሚባል ቦታ መንገድ ተዘግቶባቸዋል። ሐረር መሐል ከተማ የሚገኙ አብዛኞች ሱቆች ተዘግተው መዋላቸውን የከተማዋ ነዋሪዎች ለኢትዮጵያ ዛሬ ድረ ገጽ ገልጸዋል።
በሰሜን አቅጣጫ የሐረር ከተማ መግቢያ በኾነውና ሐማሬሳ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ወደ ከተማዋ መግባትም ኾነ መውጣት እንዳይቻል መንገድ ተዘግቶ ውሏል። ደንገጎ በሚባለውና ሐረርን፣ ድሬ ዳዋንና አዲስ አበባን በሚያገናኘው ከተማም እንዲሁ ከአንደኛው ከተማ ወደሌላኛው ሰዎች እንዳይንቀሳቀሱ ተደርጓል። ይህንን ተግባር የፈጸሙት በቡድን የተደራጁ ወጣቶች እንደኾኑ ከአካባቢው ነዋሪዎች ለመረዳት ችለናል።
በተለይም ሐረር ከተማ ውስጥ የንግድ ተቋማት ያላቸው ነጋዴዎች ሱቆቻቸውን ለመዝጋት ከተገደዱ ዛሬ ሦስተኛ ቀናቸው መኾኑ ታውቋል። ነጋዴዎቹ ሱቆቻቸውን እንዲዘጉ ማስፈራራት የደረሰባቸው ከመኾኑም በላይ በዘርና በሃይማኖት ለይተው ለጠቀሷቸው ወገኖች “እንዳትሸጡ!” የሚል መልእክትም ተላልፎ እንደነበር ከደረሰን መረጃ ለመረዳት ችለናል።
በድሬ ዳዋ ዩኒቨርሲቲ ተፈጥሮ በነበረ ግጭትና ኹክት የተማሪዎች ሕይወት እስከመጥፋት በመድረሱ ትምህርት ተቋርጦ ተማሪዎች ወደየቤታቸውና ወደየመጡበት እንዲመለሱ መደረጉ ይታወሳል። ጥር 14 ቀን ዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ትምህርታቸው እንዲቀጥሉ ጥሪ አስተላልፎ ጥቂት ተማሪዎች ወደ ባለፈው ሰኞ ጥር 18 ቀን ትምህርት መጀመራቸውን መዘገባችን አይዘነጋም። በዚህም መሠረት ተማሪዎች ከተለያዩ ክልሎች ወደ ድሬ ዳዋ መመለሳቸውን እየተመለሱ የነበረ ቢኾንም፤ ደንገጎ ላይ መንገድ ስለተዘጋባቸው ለጊዜው ጉዟቸው መስተጓጎሉ ታውቋል።
በዛሬው ዕለት በሐረር ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት ተቋርጦ መዋሉንና በጥቂት ቦታዎች ብቻ ባጃጆች ሲንቀሳቀሱ እንደነበር የከተማዋ ነዋሪዎች ለኢትዮጵያ ዛሬ አስረድተዋል።
ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ ጀምሮ በተደጋጋሚ በሐረር ከተማ ስትናወጥና ነዋሪዎችዋ ሰላም በማጣት ለሥነልቦና አለመረጋጋት እንደተዳረጉ ነዋሪዎችዋ እየገለጹ ይገኛሉ። በከተማዋ የሰው ሕይወት መጥፋት፣ የአካል ጉዳት መድረስ፣ የንብረት መውደም፣ ረብሻ፣ መንገድ መዝጋትና አድማ እየተበራከተ መምጣቱና መቆም አለመቻሉ ያሳሰባቸው ነዋሪዎች፤ “እውነት መንግሥት አለ ውይ?” የሚል ጥያቄ እየጠየቁ ይገኛሉ።
በሐረር ከተማ በያዝነው ወር የጥምቀት በዓል ሲከበር ታቦት እንዳይወጣ መደረጉና ግጭት መከሰቱ አይዘነጋም። (ኢዛ)