Ethiopian Arilines

የኢትዮጵያ አየር መንገድ

በረራውን ማቆም መፍትሔ አይሆንም የሚል አመለካከት ይዟል

ኢዛ (ረቡዕ ጥር ፳፯ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. February 5, 2020)፦ ከኮሮና ቫይረስ ክስተት ጋር ተያይዞ ሊፈጠር የሚችለውን ችግር ከግምት በማስገባት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ቻይና የሚያደርጋቸውን በረራዎች እንዲያቆም የሚለውን ውትወታ አየር መንገዱ የማይቀበለው ስለመኾኑ ተገለጸ። በረራውን ማቆም መፍትሔ አይሆንም የሚል አመለካከት ይዟል።

ከኮሮና ቫይረስ ሥርጭት ጋር በተያያዘ አየር መንገዱ ወደ ቻይና የሚያደርገውን በረራ አስመልክቶ ዛሬ የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም ከኮሮና ቫይረስ ስጋት ጋር ተያይዞ ወደ ቻይና በረራ ማቆም ዋስትና እንደማይሠጥ ገልጸዋል።

ሥራ አስፈፃሚው በግልጽ እንዳስቀመጡትም ወደ ቻይና የሚደረግን በረራ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የማያቋርጥ መኾኑን ነው።

አቶ ተወልደ ወደ ቻይና የሚደረግ በረራ ቢቆም እንኳን ወደሌሎች አገሮች የሚደረገው በረራም ከስጋት ነፃ እንደማይኾን በመጠቆም፤ የቻይና በረራዎችን ይቋረጥ የሚለው ላይ አይስማሙም።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በርካታ በረራ ከሚያደርግባቸው መዳረሻ አገራት ቻይና አንዷ ስትሆን፤ በሳምንት ከ30 - 35 በረራዎችን ወደ ቻይና የተለያዩ ከተሞች ያደርጋል።

የተለያዩ አገሮች አየር መንገዶቻቸው ወደ ቻይና እንዳይበሩ ያቀቡ ቢሆንም፤ ኢትዮጵያ አየር መንገድ በጥንቃቄ እንደሚበር፤ ከዚህም ቀደም አስታውቆ እንደነበር አይዘነጋም።

የዓለም ጤና ድርጅትም የቫይረሱን ሥርጭት አደገኝነትና አሳሳቢነት ይፋ ቢያደርግም፤ አየር መንገዶች በረራን ማቀብ ግን ተገቢ ያለመኾኑን መጥቀሱም ይታወቃል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!