ደቡብ አፍሪካ የሕብረቱ ሊቀመንበርነትን በመረከብ የአፍሪካ ሕብረት ጉባዔ ተጀመረ
 
		የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳና ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ
ደቡብ አፍሪካ ሊቀመንበርነቱን የተረከበቸው ከግብጽ ነው
ኢዛ (እሁድ የካቲት ፩ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. February 9, 2020)፦ ደቡብ አፍሪካ የወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበር በመኾን ለቀጣዩ አንድ ዓመት ለማገልገል የሚያስችላትን ኃላፊነት በመረከብ፤ 33ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ ዛሬ የካቲት 1 ቀን 2012 ዓ.ም. በአዲስ አበባ በሕብረቱ አዳራሽ ተጀመረ።
ደቡብ አፍሪካ የወቅቱን ሊቀመንበርነት የተረከበችው ከግብጽ ሲሆን፣ ይህንንም የግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ ለደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ አስረክበዋል።
“ለአፍሪካ ልማት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የጦር መሣሪያ ድምፅን ማጥፋት” የሚል መሪ ሐሳብ ይዞ የሚካሔደው ጉባዔ፤ የተለዩ ውሳኔዎች ያሳፋል ተብሎ ይጠበቃል። ከሚወያዩባቸው አጀንዳዎች ውስጥ አንዱ አህጉራዊውን የሰላምና የጸጥታ ጉዳይ የተመለከተ ነው።
ከመክፈቻ ንግግሮች በኋላ መሪዎቹ ጉባዔያቸውን የሚያካሒዱት በዝግ ነው። ጉባዔው ዛሬና ነገ የሚካሔድ ነው። (ኢዛ)



