“ሕጉንና ሕገመንግሥቱን አክብረው የሚሠሩ ፓርቲዎች መጥራት ይገባቸዋል”

ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ

“ካሉን 60 ሺህ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች (የተማሩ) አባሎቻችን የተወሰኑት በመታወቂያው ሥራ መፈለጊያና ትምህርት ቤት መግቢያ አድርገውታል፤በቀጣይ የማጥራት ሥራ እንሠራለን”

አቶ በረከት ስምዖን

“በሚቀጥሉት ዓመታት በየዓመቱ 7 ሺህ ዶክተሮችን በማስመረቅ ገበያውን በዶክተሮች ማጥለቅለቅና ተጨማሪ ማበረታቻዎችን በመስጠት ማቆየት ዕቅዳችን ነው”

የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድኃኖም

Ethiopia Zare (ቅዳሜ መስከረም ፲ (10) ቀን ፳፻፩ (2001) ዓ.ም. September 20, 2008)፦ ከሰኞ መስከረም 5 ቀን 2001 ዓ.ም. ጀምሮ በሐዋሳ ከተማ ለሦስት ቀናት በተደረገው 7ኛው የኢህአዴግ ድርጅታዊ ጉባዔ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፖርቲዎችን አስመልክተው ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ እንደገለጹት፣ ሕገመንግሥቱን በማጣቀስ ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች እንዳሉ ገልጸው፣ ሕገመንግሥታዊ ሥርዓቱን አክብረው የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች በጣም ጥቂት ናቸው ብለዋል፤ ስለዚህም ሕጉንና ሕገመንግሥቱን አክብረው የሚሠሩ ፓርቲዎች መጥራት ይገባቸዋል ሲሉ ተደምጠዋል።

 

በጉባዔው ተሳታፊ የሆኑ አንዲት ግለሰብ ፓርቲዎቹን ለማጥራት በሚል የሚሠራው ሥራ ድርጅቱ የሚቀበለውን የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት አይጋፋም? በርካታ ፓርቲዎችንስ ከጨዋታ ውጪ አያደርግም ወይ? በሚል ጥያቄ አቅርበዋል።

 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዚህ ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ፣ በመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ውስጥ ብዙ ፓርቲዎች ይኑሩ ወይም አይኑሩ የሚለው ገና ብዙ ውይይት የሚያስፈልገው ነው ብለዋል።

 

በሌላ በኩል በዚሁ ስብሰባ ላይ ለኦሮሚያ ሕብረት ሥራ ባንክ ተፈቅዶ፣ ሌሎች ሕብረት ሥራ ባንክ ሆነው ለመቋቋም ሲጠይቁ ግን መከልከላቸውን በመጥቀስ ለምን እንዲህ እንደተደረገ አንድ ሌላ ተሰብሳቢ ላነሱት ጥያቄ የብሔራዊ ባንክ ገዢ መልስ ሰጥተዋል።

 

የባንኩ ገዢ አቶ ተክለወልድ አጥናፉ ጥያቄውን ሲመልሱ፣ የኦሮሚያ ሕብረት ሥራ ባንክ ለመቋቋም ሲጠይቅ እንደማንኛውም ባንክ መሆኑንና በኋላም ሌሎች ሕብረት ሥራ ማኅበራት ባንክ ሆነው ለመቋቋም ሲጠይቁ ባንኩ ከስሙ ውጪ ሥራውን እየሠራ ያለው እንደማንኛውም ባንክ መሆኑን በመግለጽ፤ ባንክ ሆነው ለመቋቋም የሚያስችላቸው ሕግ እንደሌለ እየተገለጸላቸው መከልከሉን አስረድተዋል።

 

በስብሰባው ማጠናቀቂያ ላይ በየዕለቱ መግለጫ ይሰጡ የነበሩት አቶ በረከት ስምዖን ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ደግሞ 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን አባላት እንዳላቸው፣ ከዚህ ውስጥ 60 ሺህ አባላቱ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች (የተማሩ) እንደሆኑና ከነዚህ ውስጥ የተወሰኑት በመታወቂያው ሥራ መፈለጊያና ትምህርት ቤት መግቢያ አድርገውታል ሲሉ ወቅሰዋል። በቀጣይም የአባልነት ግዴታቸውን ለመወጣት የሚችሉትንና የማይችሉትን በመለየት የማጥራት ሥራ እንሠራለን ሲሉ አቶ በረከት አስረድተዋል።

 

የአባላት ቁጥር መብዛትን በሚመለከት ኢህአዴግ እየሠራ ያለው ሥራ የተቃዋሚ ፓርቲዎችን መንገድ እያጠበበ አይደለም ወይ? በሚል ከጋዜጠኞች ተጠይቀው “እኛ እነሱ መሠረት ያረጉትን የኅብረተሰብ ክፍል አይደለም አባል እያደረግን ያለነው፣ የገጠርና የከተማውን ክፍል ነው” በሚል መልስ ሰጥተዋል። “ታዲያ ምን ተረፋቸው?” በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ ተቃዋሚዎች መሠረት ያደረጉት የደርግ ሥርዓት ተጠቃሚዎች የነበሩትንና አሁንም የደርግ ጽንሰ ሃሳብ ናፋቂዎችን ነው ሲሉ አቶ በረከት መልሰዋል።

 

በተጨማሪም በማስተርስና በፒ.ኤች.ዲ. ትምህርት ለመማር የሚፈልጉ የኢህአዴግ አባል ካልሆኑ ዕድሉ አይሰጣቸውም፣ በሚል አዲስ ነገር ጋዜጣ ላይ የተዘገበውን በሚመለከት ተጠይቀው የቀረበው ዘገባ የሰነድ ትርጉም አፈታት ችግር እንደነበረበት በመግለጽ፣ ኢህአዴግ በወረዳ ላይ ያሉ የመካከለኛ ደረጃ አመራር ሰጪዎችን እየመለመለ በማስተርስና በፒ.ኤች.ዲ. ያሰለጥናል የሚል ዕቅድ ተያዘ እንጂ ሌሎች ገብተው እንዳይማሩ ያደርጋል አይልም ብለዋል።

 

የጤናን ጉዳይ በተመለከተ ማብራሪያ የሰጡት የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ዶ/ር ቴዎድሮስ አድኃኖም አሁን ባለው ሁኔታ በየዓመቱ እስከ 250 የሚሆኑ ዶክተሮችን ማሠልጠናቸውን ገልጸው፤ በቅርቡ በዓመት 1 ሺህ ከዚያም በዓመት 7 ሺህ ዶክተሮችን በየዓመቱ ማሠልጠን እንደሚጀመር ጠቁመዋል። በዚህም ገበያውን በማጥለቅለቅና ተጨማሪ ማበረታቻዎችን በመስጠት ዶክተሮቹን ለማቆየት እንደታሰበ አስታውቀዋል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ