የኮረና ቫይረስ 16 ተጠርጣሪዎች ተመርምረው ነፃ ኾነዋል
ኖቭል ኮሮና ቫይረስ
465 ባሉበት ኾነው ክትትል እየተደረገላቸው ነው
ኢዛ (ሰኞ የካቲት ፱ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. February 17, 2020)፦ ኮቪድ-19 የሚል ስያሜ እየተሠጠው ያለው የኮሮና ቫይረስ በሽታ እስከ የካቲት 8 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ በኢትዮጵያ ወረርሽኙ ያልተከሰተ መኾኑ ተገለጸ።
16 የሚኾኑ የበሽታው ምልክቶች በማሳየታቸው በለይቶ ማቆያ እንዲቆዩ ተደርጐ እንደነበርም ታውቋል።
የጤና ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በጋራ ይፋ ባደረጉት መረጃ፤ ከጥር 1 ቀን 2012 ጀምሮ እስከ የካቲት 8 ቀን ድረስ በደረሱ 51 ጥቆማዎች (ጭምጭምታ ሪፖርቶች) መሠረት በተደረገ ማጣራት፤ 16ቱ የበሽታው ምልክቶችን በማሳየታቸውና የቻይና ጉዞ ታሪክ ስላላቸው በተለያየ ጊዜ በለይቶ ማቆያ ማዕከል እንዲቆዩ ተደርጓል።
16ቱም የላብራቶሪ ምርመራ ተደርጐላቸው ከቫይረሱ ነፃ መኾናቸውንም ይኸው ትናንት የወጣው የጤና ሚኒስቴር መግለጫ ያመለክታል።
በዚሁ መግለጫው ጨምሮ እንደገለጸው፤ ከጥር 15 ቀን ጀምሮ በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ 125,850 በላይ የሙቀት ልየታ ያለፉ ኾነዋል። ከእነዚህ መንገደኞች ውስጥ 3,538 በሽታው ሪፖርት ከተደረገባቸው አገሮች የመጡ ናቸው። 465 የሚኾኑት ደግሞ ባሉበት ቦታ ኾነው የጤና ክትትል እየተደረገላቸው መኾኑንም ይጠቅሳል።
ጤና ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ይህንን መግለጫ እስካወጡበት ጊዜ ድረስ በዓለም አቀፍ ደረጃ 51,857 የሚኾኑ ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን፤ በቫይረሱ ተጠቅተው የሞቱት ቁጥር 1,669 ደርሷል።
እስካሁን ባለው መረጃ በአፍሪካ ቫይረሱ የተጠቃ ሰው የተገኘው በግብጽ መኾኑን የሚያሳየው ይኸው መረጃ፤ በግብጽ የተመዘገበው ተጠቂ አንድ ነው። (ኢዛ)



