ባለሀብቱ ኤርሚያስ አመልጋና የአብኑ ክርስቲያን ታደለን ጨምሮ 63 ሰዎች ክሳቸው ተቋረጠ
ባለሀብቱ ኤርሚያስ አመልጋና (በግራ)፣ የአብኑ ክርስቲያን ታደለ (በቀኝ)
ከእስር ተፈትተዋል
ኢዛ (ማክሰኞ የካቲት ፲፯ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. February 25, 2020)፦ ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ከመጡ ወዲህ በተለያዩ ወንጀሎች ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር የነበሩና በእስር ላይ ኾነው ጉዳያቸውን ሲከታተሉ የቆዩ 63 ግለሰቦች ክሳቸው የተቋረጠላቸው መኾኑ ይፋ ተደረገ።
ክሳቸው እንዲቋረጥላቸው ውሳኔ ከተሠጣቸው ውስጥ ከሜቴክ ጋር በተያያዘ በሙስና ታስረው የነበሩ፣ ከሰኔ 16ቱ የመስቀል አደባባይ የቦምብ ጥቃት እጃቸው እንደነበር ተጠርጥረው ታስረው የነበሩ ይገኙበታል።
ከዚህም ሌላ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ግጭት በማስነሳት ተከሰው የነበሩ ተጠርጣሪዎችም ከ63ቱ ውስጥ ይገኛሉ።
ሰኔ15 ቀን በአማራ ክልል “መፈንቅለ መንግሥት” ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው ከነበሩት የተወሰኑት ክሳቸው ተቋርጧል። በቤኒሻንጉል፣ በሱማሌ፣ በሲዳማ ክልል ተፈጥረው በነበሩ ግጭቶች እጃቸው አለበት ተብለው የተጠረጠሩም ይገኙበታል። የኤጄቶ አመራሮች የነበሩና የሲዳማ ሚዲያ ኔትዎርክ ባለቤት የነበሩትም ክሳቸው እንዲቋረጥ ከተደረጉት ውስጥ ይገኛሉ።
የጤንነት ችግር ያለባቸው፣ የወንጀል ተሳታፊነታቸው አነስተኛ የኾኑ፣ ከልጆቻቸው ጋር የታሰሩና በመሳሰሉ ምክንያቶች ክሳቸው የተቋረጠም አለ። በዋናነት ግን አገርን የሚጠቅም ከመኾኑ ጋር ተያይዞ የተወሰነ መኾኑ በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ተገልጿል። ለአገራዊ አንድነትና ለለውጡ የሚኖረውን አስተዋጽኦ ከግምት በማስገባ፤ እንዲሁም የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ሲባል እርምጃው መወሰዱ ተገልጿል።
ዛሬ በዓቃቤ ሕግ ይፋ በኾነው መረጃ ክሳቸው ከተቋረጠላቸው መካከል የቀድሞ የኢንሳ ምክትል ዳይሬክተር ኮሎኒል ቢኒያም ተወልደ አንዱ ናቸው። የሪቬራ ሆቴል ባለቤት የነበሩትና ይህንን ሆቴል ከሜቴክ ጋር በመሳጠር ባልተገባ ዋጋ ሽጠዋል በሚል የተጠረጠሩት የዓለም ገነት ቆሮቆሮ ፋብሪካ ባለቤት አቶ ዓለም ፍጹም ይገኙበታል። አቶ ዓለም ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ይፈጃል የተባለ የሼራተን ሆቴል አባል የኾነ ሆቴል ቦሌ አካባቢ እየገነቡ ባለበት ወቅት ነው የታሰሩት።
አቶ ኤርሚያስ አመልጋ
አቶ ኤርሚያስ አመልጋ ዛሬ የተቋረጠው የክስ መዝገባቸው እንደሚያመለክተው፤ የኢምፔሪያል ሆቴልን ከሜቴክ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመመሳጠር ሆቴሉ ሊያወጣ በማይችል ዋጋ እንዲገዛ አድርገዋል በሚል ነው። ሕንጻውን ሜቴክ ለእንግዳ ማረሪያነትና ለቢሮነት ሲጠቀምበት የነበረ ሲሆን፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ለቢሮነት እየተገለገለበት እንደሚገኝ ይነገራል።
ክሱ ባለፈው ዓመት ጥር 2011 ዓ.ም. ሲመሠረት፤ ከ41 እስከ 51 ሚሊዮን ብር የሚገመተውን የኢምፔሪያል ሆቴል አቶ ኤርሚያስ በ72 ሚሊዮን ብር በመሸጥ 21 ሚሊዮን ብር ጉዳት አድርሰዋል በሚል እንደነበር ይታወሳል። ሽያጩ የተካሔደው በ2003 ዓ.ም. ነበር። በአሁኑ ወቅት ይህ የቀድሞው ኢምፔሪያል ሆቴል ስሙ ተቀይሮ “አሞራው ሕንጻ” የሚባል ሲሆን፤ ሕንጻው በገቢዎች ሚኒስቴር ተይዞ ይገኛል። በቅርቡም ገቢዎች ሚኒስቴር ሕንጻውን ከሜቴክ ጠቅልሎ ይረከባል ተብሎ ይጠበቃል።
ሌ/ኮሎኔል ቢኒያም ተወልደ
ሌ/ኮሎኔል ቢኒያም ተወልደ ተጠርጥረው በነበረው ወንጀል ሲከሰሱ የክሱ ጭብጥ የተለየ ቢኾንም፤ ከዚህ ውስጥ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ከ72 ሚሊዮን ብር በላይ የሥልጠና ግዥ ፈጽመዋል የሚል ይገኝበታል።
ሌ/ኮ ቢኒያም ከነባለቤታቸው ምንጩ ያልታወቅ ሀብት አካብተዋል፣ በሙስና የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ በማቅረብ በሙስና ወንጀል መከሰሳቸው ይታወሳል።
አቶ ክርስቲያን ታደለ
በዛሬው ዕለት ክሳቸው የተቋረጠላቸው ሌላኛው ተጠርጣሪ የነበሩት የአብን የፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ክርስቲያን ናቸው። አቶ ክርስቲያን ታደለ ተጠርጥረው የታሰሩበት ምክንያት ወጣቶችን መሣሪያ በማስታጠቅና በማደራጀት ከሚል ድርጊት ጋር በተያያዘ ነበር። አቶ ክርስቲያን በታሰሩበት ወቅት የአብን ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የነበሩ ሲሆን፤ በእስር እያሉ ፓርቲያቸው የፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ አድርጎ በሥራ አስፈፃሚነት እንደመረጣቸው መዘገባችን አይዘነጋም።
ከአቶ ክርስቲያን ሌላ ዛሬ ክሳቸው እንዲቋረጥ ከተደረጉት ውስጥ፤ አቶ በለጠ ካሳ የአብን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ፣ አቶ ሲሳይ አልታሰብ የአብን ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የነበሩ፣ አቶ አማረ ካሳ የአብን የአዲስ አበባ የሕዝብ ግንኙነት አባል የነበሩ ናቸው። እነዚህ የአብን አመራሮችና ሌሎች ዛሬ ክሳቸው የተቋረጠላቸው ተጠርጣሪዎች ከእስር መፈታታቸው ታውቋል። (ኢዛ)
ስም ዝርዝር
በዛሬው ዕለት (ማክሰኞ የካቲት 17 ቀን 2012 ዓ.ም.) ስማቸው በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ክሳቸው የተቁረጠውና ከእስር እንዲፈቱ የተደረጉት 63 ግለሰቦች ስም ዝርዝር እንደሚከተለው ነው፤
1. ሌ/ኮ/ ቢኒያም ተወልደ፣
2. ሌ/ኮ/ል ሰላይ ይሁን፣
3. ሌ/ኮ/ል ጸጋዬ አንሙት፣
4. ኮ/ል ሸጋው ሙሉጌታ፣
5. ኮ/ል ግርማ ማንዘርጊያ፣
6. ኮ/ል ዙፋን በርሄ፣
7. ኮ/ል አሰመረት ኪዳኔ፣
8. ሻ/ል ይኩኖአምላክ ተሰፋዬ፣
9. አቶ ዓለም ፍጹም፣
10. አቶ ሰለሞን አብርሃ፣
11. አቶ ሰመረ ኃይለ፣
12. አቶ ክፍላይ ንጉሴ፣
13. ሌ/ኮ/ል መንግሥቱ ከበደ፣
14. ሌ/ኮ/ል እሥራኤል አሰፋው፣
15. ሌ/ኮ/ል ከተማ ከበደ፣
16. ሌ/ኮ/ል ለተብርሃን ደሞዝ፣
17. አቶ ኡስማን ከበደ፣
18. ሌ/ኮ/ል ዋቅቶላ አዲሱ፣
19. ሌ/ኮ/ል ታቦር ኢዶሳ፣
20. ሻ/ል ዮሐንስ ትኬሳ፣
21. ወ/ሮ ወላንሳ ገ/ኢየሱስ፣
22. ሻ/ቃ ረመዳን ለጋስ፣
23. አቶ ሙሉጌታ ሰይድ፣
24. አቶ ዋሴዕ ሳድቅ፣
25. አቶ ሲሳይ ደበሌ፣
26. አቶ አክሊሉ ግርማይ፣
27. ወ/ሮ ራህማ መሐመድ፣
28. ወ/ሮ ዘምዘም ሐሰን፣
29. ኮ/ር ፋሩቅ በድሪ፣
30. አቶ አሳጥረው ከበደ፣
31. አቶ ሲሳይ አልታሰብ፣
32. አቶ አበበ ፋንታ፣
33. አቶ አሰቻለው ወርቁ፣
34. አቶ ተሾመ መለሰ፣
35. አቶ ዓለምነህ ሙሉ፣
36. አቶ ከድር ሰይድ፣
37. አቶ አዲስ አማረ፣
38. አቶ አማረ ብሌ፣
39. አቶ ክርስቲያን ታደለ፣
40. አቶ በለጠ ካሳ፣
41. አቶ ሚፍታህ ሸምሱ፣
42. ዶ/ር ማቴ ማንገሻ፥
43. አቶ ታሪኩ ለማ፣
44. አቶ ጌታሁን ዳጉይ፣
45. አቶ በላይ በልጉዳ፣
46. ሪ/ፓ/ር አመሉ ጣሚሶ፣
47. አቶ ተፈራ ቄንፈቶ፣
48. ረዳት ፕሮፈሰር ተሰማ ኤልያስ፣
49. አቶ አማኑኤል በላይነህ፣
50. አቶ አዲሱ ቃሚሶ፣
51. ሱ/ኢ/ አሰገል ወ/ጊዩርጊስ፣
52. ሱ/ኢ/ አሰፋ ኪዳኔ፣
53. ሱ/ኢ/ ገ/እግዚአብሔር ገ/ሃዋርያት፣
54. አቶ ግርማ አቡ፣
55. አቶ አብዱልሙኒየር አብዱልጀሊስ፣
56. አቶ ቶፊቅ አብዱልቃድር፣
57. አቶ ከማል መሐመድ፣
58. ኮ/ር ኡስማን አሕመድ፣
59. ኮ/ር ኤዶሳ ጎሽ፣
60. አቶ ባበከር ከሊፋ፣
61. ዋ/ሳ/ እቴነሽ አርፋይኔ፣
62. አቶ ኤርሚያስ አመልጋ፣
63. አቶ ሙሉጌታ ሰይድ።



