ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ፣ ረዳት ፕ/ር በለጠ ሞላ (በቀኝ)

የንቅናቄውን ሊቀመንበር የነበሩት ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ (በግራ)፣ አዲሱ ሊቀመንበር ረዳት ፕ/ር በለጠ ሞላ (በቀኝ)

ምክትላቸው የነበሩት በለጠ ሞላ (ረዳት ፕ/ር) ቦታውን ተረክበዋል

ኢዛ (ሰኞ የካቲት ፲፮ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. February 24, 2020)፦ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የእስካሁኑን የንቅናቄውን ሊቀመንበር ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔንና ሌሎች አመራሮችን በአዲስ የተካበትን ምርጫ ማካሔዱ ተገለጸ።

አብን የካቲት 14ና 15 ቀን 2012 ዓ.ም. በደብረ ብርሃን ከተማ ባካሔደው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ባደረገው ምርጫ ረዳት ፕ/ር በለጠ ሞላን ሊቀመንበር፣ አቶ ዩሱፍ ኢብራሒምን ምክትል ሊቀመንበር አድርጎ መርጧል። መረጃዎች እንደሚያሳዩት አዲሱ ሊቀመንበር እስካሁን ምክትል ሊቀመንበር ኾነው ሲያገለግሉ የነበሩ ናቸው።

አብን በዚህ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔው ላይ 45 ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን ከመምረጠ በኋላ፤ የፓርቲውን ሊቀመንበሩንና ምክትል ሊቀመንበሩን ጨምሮ፤ ዘጠኝ ሥራ አስፈፃሚዎችን ኃላፊነት አጽድቋል። በዚህ መሠረት ቀሪዎቹ ሰባቱ ሥራ አስፈፃሚዎች፤

1. አቶ አዲስ ሐረገወይን - የፖሊሲ ስትራቴጂ ኃላፊ፣
2. አቶ ጣሂር ሞሐመድ - የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ፣
3. ዶ/ር ቴዎድሮስ ኃ/ማርያም - የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ግንኙነት፣
4. አቶ ጋሻው መርሻ - የአደረጃጀት ጉዳይ ኃላፊ፣
5. አቶ መልካሙ ፀጋዬ - የጽሕፈት ቤት ኃላፊ፣
6. አቶ ጥበበ ሰይፈ - የሕግና ሥነምግባር ኃላፊ፣
7. አቶ ክርስቲያን ታደለ - የፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ መኾናቸው ታውቋል።

አቶ ክርስቲያን ታደለ የአብን የሥራ አስፈፃሚ አባልና የፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ ኾነው የተመረጡት በሌሉበት ሲሆን፣ አቶ ክርስቲያን ከሰኔ 15ቱ የባህር ዳር ግድያ ጋር በተገናኘ በእስር ላይ እንዳሉ አይዘነጋም። አብን አቶ ክርስቲያን የታሰሩት በፖለቲካ መኾኑን በመጥቀስ በተደጋጋሚ ከእስር እንዲፈቱ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ እንደቆየ ይታወቃል።

ምናልባትም አቶ ክርስቲያን በዛሬው ዕለት በተደመጠውና የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ምሕረት ካደረገላቸው 60 ሰዎች ውስጥ አንዱ ይኾናሉ ተብሎ ይጠበቃል። ምሕረት የተደረገላቸው ሰዎች ዝርዝር በነገው ዕለት ይፋ እንደሚኾን ተደምጧል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ