PM Abiy Ahmed

ጠቅላይ ሚኒስትርና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ

“የሠራዊታችን አመራሮችና አባላት ያላቸው ሁሉ ለአገራቸው ለመሥጠት ፍጹም ቆራጦች ናቸው” ዶ/ር ዐቢይ

ኢዛ (ሰኞ የካቲት ፴ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. March 9, 2020)፦ ጠቅላይ ሚኒስትርና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ከአገር መከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ አመራሮች ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ምክክር አደረጉ።

ዛሬ የካቲት 30 ቀን 2012 ዓ.ም. በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በተደረገው ምክክር ላይ በተለያዩ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ምክክር ማድረጋቸውን የሚጠቁመው መረጃ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ “የሠራዊታችን አመራሮችና አባላት ያላቸው ሁሉ ለአገራቸው ለመሥጠት ፍጹም ቆራጦች ናቸው” ማለታቸውን ይጠቅሳል።

ምክክሩን የተመለከተ ዝርዝር ነገር ባይገለጽም፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፌስቡክ ገጻቸው፤ “ብሔራዊ የመከላከያ ሠራዊታችን አመራርና አባላት ለአገራቸው ያላቸው ፍቅር አስደናቂ ነው። ያላቸውን ሁሉ ለአገራቸው ለመሥጠት ፍጹም ቆራጦች ናቸው። ዛሬ ጠዋት ከአመራሮቹ ጋር የነበረኝ ስብሰባ በሠራዊታችን ያለኝን መተማመን የሚጨምር ነው” ብለዋል።

“የቀጠናውን ሰላም በትኩረት መከታተል ይገባል” ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሰሞኑን በሰሜን ዕዝ ለከፍተኛ መኮንኖችና ለተመጣጣኝ የስታፍ ክፍል ኃላፊዎች የተሠጠ ሥልጠናን መጠናቀቅ ተከትሎ፤ የጦር ኃሎች ምክትል ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ፤ “የቀጠናውን ሰላም በትኩረት መከታተል ይገባል” ብለዋል።

የአገር መከላከያ ሠራዊት በፌስቡክ ገጹ እንደጠቀሰው፤ የአገር ውስጥ ወቅታዊ የጸጥታ ተግዳሮቶች ሳንገደብ በአጎራባች አገሮች የሚታየውን ወቅታዊ የፖለቲካና ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን በትኩረት መከታተል እንደሚገባ መግለጻቸውንም አመልክቷል።

“ኢትዮጵያ ምሥራቅ አፍሪካ ከግጭት ነፃ የኾነ አካባቢ እንዲኾን አበክራ እየሠራች ትገኛለች” ያሉት ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ፤ በተለይ አገራችን ኢትዮጵያ ብሔራዊ ሀብቶቿን ለመጠቀም በምታደርገው ጥረት ጥቅማቸው የተነካባቸው የሚመስላቸው ሌሎች አገሮች፤ በፕሮጀክት ግንባታ ላይ ሳይኾን፤ በውስጣችን በሚፈጠሩ የሰላም ችግሮች እንድንጠመድና ግንባታዎች እንዲጓተቱ በእጅ አዙር የሚሠሩ ኃይሎች ሊኖሩ ይችላሉም ብለዋል።

ዘገባው አያይዞም፤ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ላይ አሁን ያለው የተፋሰሱ አገሮች ከግንባታውና ውኃ አሞላሉ ዙሪያ እያደረጉት ባለው ድርድር፤ የኢትዮጵያን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ በመኾኑ፤ አገራችን ሀብቷን ለመጠቀም የራሷ እርምጃ በምትወስድበት ወቅት፤ ሰላሟን ለማደፍረስ የቻሉትን ሁሉ ሊያደርጉ ስለሚችሉ፤ ሠራዊታችን ከሕዝቡ ጋር በመኾን አጽንኦት ሠጥቶ ሊከታተል ይገባልም ማለታቸውን ዘገባው አመልክቷል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ