ከሐረሪ ማረሚያ ቤት እስረኞች ለማምለጥ ያደረጉት ሙከራ መክሸፉ ተነገረ

ሐረር ከተማ
በእስረኞች ማደሪያ 180 ሞባይሎች ተይዘዋል
ኢዛ (እሁድ መጋቢት ፳፯ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. April 5, 2020)፦ በሐረሪ ክልል ማረሚያ ቤት ዛሬ መጋቢት 27 ቀን ጠዋት ላይ የሕግ ታራሚዎች የማረሚያ ቤቱን በራፍ በመገንጣጠል ለመውጣት ያደረጉት ሙከራ መክሸፉን የማረሚያ ቤቱ ኮሚሽነር ገልጸዋል።
ከማረሚያ ቤቱ ለማምለጥ የሕግ ታራሚዎች ሙከራ ከማድረጋቸው ቀደም ብሎ በማረሚያ ቤቱ ውስጥ ግርግር ተፈጥሮ የነበረ ሲሆን፣ ከግቢው ከመውጣታቸው በፊት ሙከራውን ማክሸፍ ተችሏል ተብሏል።
ሙከራው ከከሸፈ በኋላ ታራሚዎች የማደሪያ ክፍሎች ውስጥ በተደረገ ፍተሻ 180 ሞባይሎችና በርካታ የቅድመ ክፍያ ካርዶች መያዛቸውም ታውቋል። እነዚህ ዕቃዎች እንዲቃጠሉ ተደርጓል ተብሏል። ዛሬ የተደረገውን የማምለጥ ሙከራ ያቀነባበሩ ምርመራ እየተደረገባቸው ነው ተብሏል። (ኢዛ)