የትግራይ ክልል ለ15 ቀን ያለውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወደ ሦስት ወር አራዘመ
የሕወሓት ሊቀመንበርና የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል
ከመጋቢት 17 ቀን ጀምሮ ታሳቢ ተደርጎ የሚቀጥል ነው
ኢዛ (ሐሙስ ሚያዝያ ፩ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. April 9, 2020)፦ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ለ15 ቀን ተግባራዊ የሚደረግ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጥቶ የነበረው የትግራይ ክልል ምክር ቤት፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለሦስት ወራት እንዲራዘም ወሰነ።
ምክር ቤቱ ዛሬ ሚያዝያ 1 ቀን ባካሔደው አስቸኳይ ጉባዔ፤ በተለያዩ አገሮች የቫይረሱ ሥርጭት በፍጥነት እየጨመረ በመምጣቱና አስጊ ደረጃ ላይ በመኾኑ፤ በሽታውን ለመከላከል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተፈፃሚ የሚኾንበትን ጊዜ ወደ ሦስት ወር እንዲራዘም ወስኗል።
ይህም ውሳኔ ከመጋቢት 17 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ታሳቢ ተደርጎ የሚቀጥል ይኾናል። በዚሁ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተፈፃሚ የሚደረጉ ድንጋጌዎች ላይ በመነጋገርም፤ እንዲተገበሩ ውሳኔ ማሳለፉን ለማወቅ ተችሏል። (ኢዛ)



