ትራምፕ እንደዛቱት አደረጉት
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ (በግራ)፣ የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ዶክተር ቴዎድሮስ አድኃኖም (በቀኝ)
ለዓለም ጤና ድርጅት የ400 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እንዳይሠጥ አዘዙ
ኢዛ (ረቡዕ ሚያዝያ ፯ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. April 15, 2020)፦ ከኮሮና ቫይረስ ወረሽኝ ጋር በተያያዘ በዓለም ጤና ድርጅት ላይ ጥርሳቸውን የነከሱትና በአደባባይ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተርን ሲወቅሱ የሰነበቱት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ አሜሪካ ለድርጅቱ ታደርግ የነበረውን የገንዘብ ድጋፍ እንድታቋርጥ ትእዛዝ ሠጡ።
የዓለም የጤና ድርጅት የኮሮና ቫይረስ ሥርጭትን ለመከላከልና ከዚሁ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ኃላፊነቱን አልተወጣም በማለት በተደጋጋሚ ወቀሳ በማቅረብ ለድርጀቱ አሜሪካ የምትሠጠውን የገንዘብ ድጋፍ እንደምታቋርጥ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ዝተው እንደነበር አይዘነጋም። ትራምፕ ድርጅቱ ያልተገባ አስተዳደር ተከትሏል፤ በቻይና ቫይረሱ ከታየ በኋላ ሥርጭቱ እንዲሸፋፈን ተደርጓል ብለው ከስሰዋል።
በዚሁ መሠረት አሜሪካ ለድርጅቱ የምትሠጠውን የ400 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እንዳይሠጥ አዘዋል። አሜሪካ በዓመት ለድርጅቱ ትሠጥ የነበረው ገንዘብ ከዓለም ጤና ድርጅት ዓመታዊ በጀት 15 በመቶ ይኾናል።
የትራምፕ ውሳኔ ግን ተገቢነት የሌለውና ወቅቱን ያልጠበቀ ተብሎ እየተተቸ ነው። በዚህ ወቅት የኮሮና ቫይረስ ሥርጭትን ለመከላከል እስከ አንድ ቢሊዮን ዶላር ያስፈልገኛል ብሎ ይፋ ባደረገበት ወቅት መኾኑ ደግሞ፤ ቫይረሱን ለመከላከል የሚደረገው ጥረት ላይ ጫና ያሳድራል ተብሏል። በተለይ የአፍሪካ አገራት ላይ ጫናው ሊበረታ ይችላል የሚል አስተያየት እየተሠጠ ነው።
የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ዶክተር ቴዎድሮስ አድኃኖም ከትራምፕ ጋር የተገባው እሰጥ አገባ እና በእርሳቸውና በድርጅታቸው ላይ የሚቀርበው ወቀሳ ተገቢነት የሌለው መኾኑንና ኮሮና ቫይረስን ፖለቲካዊ ይዘት እንዲኖረው ማድረግ ተገቢ አለመኾኑን መግለጻቸው ይታወሳል። (ኢዛ)



