ፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም (ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ)

Trump

በጁሊየስ ቄሳር ተውኔት ውስጥ የቄሳርን ሞት ተከትሎ ጣሊያንን ሽባ የሚያደደርግ የእርስ በእርስ ጦርነት ሊከሰት እንደሚችል ሸክስፒር የማርክ አንቶኒን ገጸ ባህሪነት በመላበስ እንዲህ በማለት አስጠንቅቀው ነበር፤

“…እናም አቴ በእርሱ በኩል ከጋነም እሳት ሆኖ በመምጣት የቄሳርን መንፈስ በመላበስ የንጉሱን ድምጽ በመያዝ ለበቀል ተዘጋጅቷል። እናም እናልቅስ፣ እናም እነዚህን የጦርነት ውሾች እናስወግድ“ ብለው ነበር።

ባለፈው ሳምንት በሬፐብሊካን ጉባኤ ላይ በመገኘት ዶናልድ ትራምፕ የርፑብልካኑ እጩ ፕሬዚደንት “ለዚህ የስልጣን ቦታ ብቁ የሆንኩት መሲህ እኔ ብቻ ነኝ“ በማለት በቁጣ ለበቀል እና ለአስከፊ አደጋ መከሰት ሽንጡን ገትሮ ጮኸ!

የባዶ ጩኸት [1] ባለቤቱ ትራምፕ የሬፐብሊካን ፓርቲ እጩ ፕሬዚዳንት ሆኖ መሾሙን ከተቀበለ በኋላ ድምጹን ከፍ በማድረግ የውሻ ፊሽካውን እንዲህ በማለት ነፋ፡

“እኔ የእናንተ ድምጽ ነኝ። ለሁላችሁም መልዕክት አለኝ፡ በፖሊሶቻችን ላይ የተፈጸመው ጥቃት እና በከተሞቻችን ላይ እየተደረገ ያለው ሽብርተኝነት ህልውናችንን በአስጊ ሁኔታ ላይ ጥሎት ይገኛል።

በአሁኑ ጊዜ ሀገራችንን እያሰቃዩ ያሉት ወንጀሎች እና የኃይል ጥቃቶች በቅርብ ጊዜ ውስጥ ፍጻሜ ያገኛሉ። እ.ኤ.አ ከጥር 20/2017 ጀምሮ የደህንነት ዋስትናችን ድሮ ወደነበረበት ሰላማዊ ቦታው ይመለሳል።

በዚህ ዓመት የሀገሪቱን ወሰን በማቋረጥ የገቡ የአዲስ ሕገ ወጥ ስደተኞች ቁጥር እ.ኤ.አ በ2015 ከነበረው ጠቅላላ ብዛት በልጧል።

በአስር ሽዎች የሚቆጠሩ ሕገ ወጥ ስደተኞች በህዝባችን ደህንነት እና በሀገሪቱ ሀብት ላይ የሚያስከትሉት አሉታዊ እንደምታ ሳይታሰብ እንዲገቡ እየተደረጉ ነው።

የውጭ ንግድ ክፍተታችን 800 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል። እስቲ ይህንን አስቡ። ባለፈው ዓመት ብቻ 800 ቢሊዮን ዶላር። ይህንን መወሰን አለብን።

በአሁኑ ጊዜ በጀቱ በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛል። ፕሬዚዳንት ኦባማ የብድር እዳችንን በእጥፍ ደረጃ በማሳደግ ከ19 ትሪሊዮን ዶላር በላይ እንዲሆን አድርጎታል። እንዲሁም ዕዳው ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መጥቷል።

መንገዶቻችን እና ድልድዮቻችን እየተሰነጣጠቁ ነው፣ እንደዚሁም ሁሉ የአውሮፕላን ማረፊያዎቻችን የሶስተኛው ዓለም ሀገሮች ካሉበት ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

በሊቢያ የሚገኘው እና በዓለም ላይ የአሜሪካውያን የኩራት ቀንዲል የነበረው የቆንስላ ጽ/ቤታችን በእሳት እንዲጋይ ተደርጓል።

አሜሪካ ደህንነቷ ተቃውሷል፣ እንደዚሁም ኦባማ ሂላሪ ክሊንተንን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ሚኒስትር እንድትሆን ከወሰነ በኋላ ዓለም የተረጋጋች አይደለችም።

የሂላሪ ክሊንተን ትሩፋት የሚከተሉት ናቸው፡ ሞት፣ ውድመት፣ ሽብርተኝነት እና ደካማነት።

ትራምፕ “የእናንተ ድምጽ ነኝ” በማለት ድምጹን ከፍ አድርጎ ጮኸ።“ (ማለቱም የትራምፕ ድምጽ የእግዚአብሄር ድምጽ ነው፣ የእግዚአብሄር ድምጽ ደግሞ የሕዝብ ድምጽ ነው!)

በክሌቬላንድ ርፑብልካን ጉባኤ ላይ ባደረገው ንግግር ትራምፕ በእውነት እና በእውነታ፣ በአሜሪካ ሕገ መንግስት፣ በጨዋነት ላይ በሂላሪ ሮድሀም ክሊንተን ላይ ቆሻሻ ፖለቲካ በማራመድ የቃላት ጦርነትን አውጇል።

በተግባር ደግሞ ትራምፕ የእርስ በእርስ ጦርነትን አውጇል።

በሬፐብሊካን ጉባኤ ላይ የተደረገው የጦርነት ጩኸት ሂላሪ ክሊንተንን አለህግ ትሰቀል የሚል ነበር።

ትራምፓውያን ጥላቻን ባዘለ፣ ንዴትን በተላበሰ መልኩ የድንጋይ “አጥሩን ገንቡ” በማለት ጮኸዋል፣ አቃስተዋል! (ግንቡም ከውጭ ዓለም የሚመጡትን የነጭ ዘር ያልሆኑትን አሜሪካ አንዳይገቡ ለማድረግ ነው።)

ይህ ቀን የሬፐብሊካን ጉባኤ የምጻት ቀን ነበር።

የትራምፕ አማካሪ እና የሀምፕሻየር ግዛት ተወካይ ላንቃው እስኪነቃ ጮኋል! እናም ሂላሪ ክሊንተን የሀገር ክህደት ወንጀል የፈጸመች እና በከፍተኛ ደረጃ መጠየቅ ያለባት ሰው ናት በማለት የሞት ቅጣት ፈርዶባታል። በቀጣይነትም እንዲህ በማለትጨመረ፣ “እኔ እስከማውቀው ድረስ ይህ ድርጊት የሀገር ክህደት ጉዳይ ነው። እናም ለሀገር ክህደት ቅጣቱ አሁኑኑ በታጣቂ ወታደሮች በጥይት መደብደብ ወይም ደግሞ በኤሌክትሪክ አቃጥሎ መግደል ነው።“

“ወንድም” ቤን ካርሰን ስለፖለቲካ ምንም ዓይነት እውቀት የሌለው እና አቅመቢሱ ጨካኝ የሂላሪ ክልንተንን ስም ካጠለሸ በኋላ እንዲህ የሚል ተመሳሳይ ንግግር አሰምቷል፣ “ከባርነት ዘመን ወዲህ የኦባማ የጤና አጠባበቅ ድንጋጌ በሀገራችን የተፈጸመ የመጨረሻ መጥፎው ነገር ነው“ ብሏል።

ካርሰን ሂላሪ “የጽንፈኞች መመርያ/Rules for Radicals” እየተባለ የሚጠራው መጽሐፍ ደራሲ የሳውል አሊንስኪ ተከታይ ናት በማለት አውጇል። በመጽሐፉ የመቅድም ገጽ ላይ የእራሱን ግዛት የያዘውን እና ዋነኛ ጽንፈኛ ለሆነው ለሉሲፈር (ዳቢሎስ) እውቅና ሰጥቷል። ስለሆነም ለእነርሱ ተከታይ አርአያ የሆነችን ሰው እና ለሉሲፈር እውቅና ለምትሰጥ ሰው ለፕሬዚዳንትነት ለመመረጥ መፍቀድ ይኖርብናልን? (በፍጹም! ካርሰን የውሸት የሬፐብሊካንን ፖለቲካ በማነብነብ በየትኛው የአንድሮማ ጋላክሲ ፕላኔት አብዛኛውን ጊዜውን እንደሚያጠፋ የማውቀው ነገር የለም።)

ሳውል አሊነስኪ በድህረ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጊዜ የአፍሪካ አሜሪካውያንን የመኖሪያ አካባቢ እና የደኃ ማህበረሰቦችን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል ከችጋጎ እስከ ኒዮርክ፣ ከዚያም እስከ ሎስ አንጀለስ ድረስ ማህበረሰቡን ሲያደራጅ እና ሲያስተባብር የነበረ ታሪካዊ ሰው ነው።

የአሊንስኪ “የጽንፈኞች መመርያ/Rules for Radicals” መንገድ ጠራጊ መጽሐፍ ማህበረሰብን ለማደራጀት እንደ መጽሐፍ ቅዱስ የሚቆጠር መጽሐፍ ነው።

አሁን በህይወት የሌለው እና የወግ አትባቂ ምሁራን ምሳሌ የሆነው ዊሊያም በክለይ (ለአዲሱ የአሜሪካ ወግ አጥባቂነት መሰረት ለመጣል ብቸኛ የሆነው ሰው) በአንድ ወቅት አሊንስኪን “እጥፍ ድርብ ተደናቂ የሆነ እና የአደራጅነት ልህቅናን የተጎነጸፈ ሰው“ በማለት አወድሶታል።

ግልጽ በሆነ መልኩ ካርሰን ጭካኔን በተሞላ መልኩ ሂላሪ ክሊንተንን እንደ ሰይጣን፣ ጽንፈኛ ኢሞራላዊ የጾታ ግንኙነት ፈጻሚ አሜሪካዊ አድርጎ የመቁጠር ሙከራ አድርጎ ነበር።

ከሬፐብሊካን (ሀሳብ የለሾች አምሮ ቢስ አላልኩም) መሪዎች ስም ዝርዝር መካከል ውስጥ ያለ እና የሂላሪ ክሊንተንን ስም በማጠልሸት ላይ የሚገኘው ያገኘውን ምግብ ሁሉ አግበስባሹ ሆዳም እና በሕግ እና ስርዓት ዕጩው (ትራምፕ) ስም ሆኖ ሂላሪን በመወንጀል፣ ከስብዕና ውጭ ለማድረግ እና ስም በማጠልሸት ላይ የሚገኘው የኒው ጀርሲ ገዥ የሆነው ክሪስ ክሪስቲ አንዱ እና ዋናው ነው።

ክሪስቲ እንዲህ በማለት እንደ አቡጀዲ ተቀዷል፣ “በሶሪያ እና በሊቢያ ውስጥ ጥፋተኛ፣ በቻይና እና በሶሪያ ውስጥ ጥፋተኛ፣ እንዲሁም በዚህ በሀገር ቤት ውስጥ ደግሞ የአሜሪካንን ሚስጥሮች ለግሏ የማድረግ አደጋን ደቅና ትገኛለች“ ብሏል።
የትራምፕ አራያውያን (የጀርመን ናዚ ምርጥ ዝርያ ነን ይሉ የነበሩት) በጉባኤው ላይ ያለ የሌ የዘለፋ ዓይነት መዓት አውርደዋል! መታሰር አለባት! መታሰር አለባት! መታሰር አለባት! መታሰር አለባት! በማለት ላንቃቸው እስኪደርቅ ድረስ ሲጮሁ ነበር።

የአዮዋ ግዛት ተወካይ የሆነው ስቴቭ ኪንግ ስለነጮች የበላይነት እና ነጮች ለሰው ልጆች ስልጣኔ ሁሉ ብቸኛ አበርካቾች እንደሆኑ እና ሌሎችን ህዝቦች ሁሉ በማግለል እንዲህ በማለት ሲጮህ ነበር፣ “ታሪክን ወደ ኋላ መለስ ብላችሁ እንድትቃኙ እጠይቃለሁ፣ እናም ሌሎች ከነጭ ህዝቦች ውጭ የሆኑ ህዝቦች ያበረከቱት ስልጣኔ እስቲ የት አለ ንገሩን፣ ከነጭ ህዝቦች ውጭ ሌላ የህብረተሰብ ክፍል ያበረከተው ስልጣኔ የት አለ?“ ነበር ያለው የዘር ቫይረስ በደም ስሩ ውስጥ ተሰራጭቶ የሚገኘው ዘረኛ ሰይጣን።

እውነት ለመናገር የትራምፕ የዘለፋ ሰለባዎች ከሌላ ፓርቲ እና ከአናሳ የህብረተሰብ ክፍሎች ምንም ዓይነት ተቃውሞ አልደረሰባቸውም። ትራምፕ የእርሱ የፕሬዚዳንትነት ዕጩነት እንዳይጸድቅ ከሚታገሉት እና ወይም ደግሞ ምንም ዓይነት ይፋ ድጋፍ ለማያደርጉለት ሬፐብሊካውያን ወንድሞቹ ምንም ዓይነት ጊዜ አላጠፋም። ትራምፕ የኦሂኦ ግዛት ገዥ የሆነውን ጆን ካሲች እና በጉባኤው እና በትራምፕ ደደብ የልኡካን አባላት ላይ ምንም ዓይነት የድጋፍ ምልክት ያላሳዩትን ሌላ የፓርቲ መሪዎች፣ ሴናተሮች እና ገዥዎች ሙልጭ አድርጎ ዘልፏል። ጉባኤው ከተጠናቀቀ በኋላ የጉባኤው አባላት በጉባኤው መድረክ ላይ ለምን እንዳልተሳደቡ በመናገር የተሰማውን ጸጸት ግልጽ አድርጓል።

እ.ኤ.አ. በ2016 የተካሄደው የሬፐብሊካን ጉባኤ ሁለተኛውን የአሜሪካንን የእርስ በእርስ ጦርነት ለማካሄድ ትራምፕ ያደረገው ጥሪ ነውን?

ትራምፕ ሀገራችንን ከአፍሪካ አሜሪካውን፣ ከሙስሊሞች፣ ከአይሁዶች፣ ከስደተኞች፣ ከሴቶች፣ ከሰራተኛ ማህበራት እና ከሌሎች እናጽዳ በማለት በዕጩ ፕሬዚዳንትነት ማስተዋወቂያ ፕሮግራሙ ላይ ባልተጠቀሱት ላይ ሁሉ ቆጥቋጭ የሆነ ዘለፋ እና ቅጥፈቱን በመልቀቅ የጎሳ፣ የኃይማኖት እና የዘር ጦርነት ለመቀስቀስ ሙከራ በማረግ ላይ ነውን?

የትራምፕ የውሻ ፊሽካዎች አሜሪካ እራሷን በእራሷ የምታጠፋበት ሂደት ላይ የምትገኝ መሆኗን የሚያመላክት የምጻት ቀን ጥሪ ነው።

ትራምፕ ዕጩ ፕሬዚዳንት መሆኑን ካወጀበት ጊዜ ጀምሮ በአሜሪካ ውስጥ ስላለ ሞት እና ጠቅላላ ውድመት እንዲህ በማለት በመናገር ላይ ይገኛል፡

“በ18 ትሪሊዮን ዶላር ዕዳ ውስጥ ተዘፍቀን እንገኛለን። ምንም ያገኘነው ነገር የለም፣ በችግሮች ብቻ ነው ተተብትበን ያለነው… እየሞትን ነው። ገንዘብ እንፈልጋለን። ያጣን ሆነናል። ምንም የሌለው ህዝብ ሆነናል። በሞራል ስብዕና የበከተ ህዝብ ነው ያለን። ሀገሩን የሚሸጥ ህዝብ ነው ያለን…የአሜሪካ ህልም ሞቶ ተቀብሯል“ ነበር ያለው።
ትራምፕ ለወራት ያህል የእርሱን የውሻ ፊሽካ ፖለቲካ ሲነፋ ቆይቷል፣ ሆኖም ግን ይህንን ለማድረግ በአሁኑ ጊዜ ያለው ብቸኛው ዕጩ ፕሬዚዳንት እርሱ ነው።

ለአራት አስርት ዓመታት ያህል የሬፐብሊካን ፓርቲ የውሻ ፊሽካ ፖለቲካን በማራመድ ላይ ይገኛሉ። ሕግ እና ስርዓትን ለማስከበር ቃል ይገባሉ (በአፍሪካ አሜሪካውያን ላይ የኃይል እርምጃ ለመውሰድ የሚስጥር መግባቢያ ኮድ መሆኑ ነው)። የመንግስትን አዲሱን ስምምነት ለመሰረዝ ቃል ይገባሉ (የጤና ጥበቃን ድንጋጌ፣ የጤና እርዳታን፣ የማህበራዊ ዋስትናን እና የኦባማን የጤና ድንጋጌ ለመሰረዝ የሚደረግ የሚስጥር መግባቢያ ኮድ መሆኑ ነው) እንደዚሁም ግብር ለመቀነስ (በአሁኑ ጊዜ የናጠጡ ህብታሞች ሆነው የሚገኙትን የህብረተሰብ ክፍሎች ለመጥቀም ሲባል የሚስጥር መግባበቢያ ኮድ መሆኑ ነው።)

ነገሮችን ከመጠን በላይ አጋኖ እና አግዝፎ በመናገር ሕገ ወጥ የውጭ ዜጎችን መስመር ማስያዝ (ለስደተኞች በተለይም ላቲኖችን እንደ ወንጀለኛ ለመቁጠር የሚደረግ የሚስጥር መግባቢያ ኮድ መሆኑ ነው) እናም አሁን በቅርቡ ደግሞ “የሻሪያን ሕግ” መዋጋት (ሙስሊሞች ሽብርተኝነትን ያስፋፋሉ በማለት ለማስፈራራት የሚደረግ የሚስጥር መግባቢያ ኮድ መሆኑ ነው) በማለት በዜጎች ላይ ፍርሀትን ለማንገስ ነው።

ሮናልድ ሬጋን “ደህንነቷ የተጠበቀችው ንግስት” የሚል ምዕናባዊ ሀሳብ በማራመድ የማህበራዊ ደህንነቱን ስርዓት እንዲደርቅ ያደረጉ ጥቁር ሴቶች ናቸው የሚል ሀሳብ ያራምዱ ነበር።

እ.ኤ.አ በ1968 ትልቁ ጆርጅ ቡሽ የዊለ ሆርቶንን የውሻ ፊሽካ በመጠቀም (ጥቁር ጥፋተኛ ሆኖ ሲገኝ የእድሜ ልክ እና የሞት እንዲሁም ለዘለቄታው ከስራ የማባረር ቅጣት እንዲኖር የማድረግ) እና ጉዳዩን የዴሞክራቲክ ፓርቲ ዕጩ ፕሬዚዳንት ሆነው ከተሾሙት ከሚካኤል ዱካኪስ ጋር በማስተሳሰር የወንጀለኛ ፍትህ ስርዓቱን ተዘዋዋሪ ለማድረግ ነበር።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት የሬፐብሊካን የድምጽ ሰጭዎች ማንነት እውቅና ግፊት ደኃ አፍሪካ አሜሪካውያንን እና ሂስፓኒኮችን ከድምጽ መስጠት መብታቸው ለመከላከል የተዘየደ ዘዴ ነው። አሁን ባለፈው ሳምንት ሬፐብሊካኖች በቪርጂኒያ ግዛት የዴሞክራት ገዥ የሆኑት ቴሪ ማካሊፍ የእራሳቸውን የምህረት መብት ተጠቅመው ቀደም ሲል ወንጀለኛ የነበሩትን ዜጎች በቡድን ሆነው የመምረጥ መብታቸውን መጠቀም እንዲችሉ በማድረጋቸው በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ አድርገዋል።

ለዓመታት በዘለቁት በሬፐብሊካን ውሾች ፊሽካ እና በትራምፕ መካከል ያለው ልዩነት በጣም ትንሽ ነው። ብቸኛ ልዩነት ሆኖ የሚቀርበው የትራምፕ የውሻ ፊሽካ ለእርሱ ፓርቲ ዕጩ ፕሬዚዳንትነት ድምጽ ለመስጠት ለሚችሉ በተወሰኑ የሬፐብሊካን ፓርቲ አባላት የሚደመጡ እና የሚታቀፉ የመሆናቸው ጉዳይ ነው።

ትራምፕ ሞላጫ ውሸታም እና ስሜታዊ አምባገነን ነው። መንከን እ.ኤ.አ በ1926 “የዴሞክራሲ ማስታዋሻዎች/Note on Democracy“ በሚል ርዕስ ባሳተሙት መጽሐፋቸው ማንም በአሜሪካ ዴሞክራሲ ላይ ጥልቅ ግንዛቤ እንዲኖረው የፈለገ ሰው መጽሀፉን ማንበብ እንዳለበት ጠቁመዋል። መንከን በባዶ ጭንቅላት አታላይ ባዶ ቃላት ፖለቲከኛ አሜሪካንን እንደገና ታላቅ እናደርጋታለን በሚል አስመሳይ የብሄርተኝነት ስሜትን በሚሰብክ ቀጣፊ አሜሪካውያን ሰበብ አሜሪካውያን መታለል እንደሌለባቸው ማስጠንቀቂያ ሰጥተው ነበር!

ከአንድ መቶ ዓመታት ገደማ በፊት መንከን የአሜሪካንን ፕሬዚዳንታዊ የፖለቲካ መንገድ አቅጣጫ በሚገባ አስተዋሉ።

መንከን (“የባልቲሞር ብልህ ሰው” “የአሜሪካ ቮልታየር”) ስለአሜሪካ ፖለቲካውያን ወይም ደግሞ ስለድምጽ ሰጭዎችም ቢሆን ብዙ ነገር የሚያስቡ አልነበሩም። የአሜሪካ የፖለቲካ ሂደት መቋጫ የሌለው እርባና ቢስ ንግግር በሚያደርጉ እና የውሸት ፖለቲከኞች የተሞላ መሆኑን ያስቡ ነበር። የአሜሪካ ድምጽ ሰጭዎች ትክክለኛ ያልሆኑ መርሆዎችን ለሚሰብኩ እና ደደብ ለሆኑ ስሜታዊ አምባገነን ሰዎች ሰለባ እንደሚሆኑ ያምናሉ። መንከን ስሜታዊ የሆኑ አምባገነን ሰዎች የህዝቡን ፍርሀት እንዴት አድርገው ማነሳሳት እንደሚችሉ ብቻ አይደለም የሚያውቁት፣ ሆኖም ግን ከዚህም በተጨማሪ ምቀኞችን እንዴት ማፍራት እንደሚችሉ፣ ደህና ሰዎችን እንዴት መጥላት እንደሚቻል እና በደህና ሰዎች ላይ እንዴት አድርጎ ጥላቻን መፍጠር እንደሚቻል ጭምር ነበር።

መንከን በነጻነት ጉዳይ ላይ ትንሽ ፍላጎት ስላለው ህዝብ እና በእርግጠኝነት ነጻ ሲሆን ደስተኛ በማይሆነው፣ ምቾት በማይሰማው እና በመጠኑም ቢሆን በፍርኃት በተዋጠው እና ተስፋ በሌለው መልኩ ብቸኝነት ተጠናውቶት በሚገኘው የአሜሪካ ድምጽ ሰጭ ህዝብ ላይ እምነት ሊጣልበት የሚችል አይነት አመለካከት የላቸውም። አብሮ ረዥም ጉዞ የሚጓዝ እና የመንጋዎቹን ሽታ የሚያሸት ከእረኞች ጋር አብሮ የመጓዝ ፈቃደኝነት ይኖረዋል። እንደዚሁም ሁሉ የተግባራዊ ፖለቲካ አጠቃላይ ዓላማም ህዝቡን እንዲፈራ በማድረግ (ስለሆነም ጫጫታው በሰላም እንዲመራ ማስቻል ነው) እና ፍርሀትን ማለቂያ በሌለው መንገድ በመልቀቅ ሁሉም ምዕናባዊ በሆነ መልኩ እንዲመራ ማድረግ ነው።

በነብያዊ የቋንቋ አጠቃቀም መንከን እንዲህ የሚል ምልከታ አድርገዋል፣ “ዴሞክራሲ ፍጹም እየሆነ በሚሄድበት ጊዜ የፕሬዚዳንቱ ቢሮ ወካይ ይሆናል፣ በርካታዎች እና በርካታዎችን ይቀርባል፣ የህዝቡን የልብ ትርታም ያዳምጣል። ወደ መልካሙ እና ትክክለኛው ሀሳብ እንሄዳለን። በአንድ ታላቅ እና ታዋቂ በሆነ ቀን በአሜሪካ ያሉ ህዘቦች በመጨረሻው የፍላጎታቸውን ያገኛሉ። እናም ኋይት ሀውስ ዉስጥ ደደቦች ይገባሉ” ነበር ያሉት።

እዩልኝ እመኑልኝ ከሚለው ፍጡር በቴሌቪዥን ከሚታይ ተውኔት ሰሪ እና በቀጣይ ወደ ኋይት ሀውስ ለመግባት ከሚቅበጠበጠው ከዶናልድ ትራምፕ የበለጠ ማንም ቢሆን ታላቅ ደደብ ሊታሰብ አይችልም።

የዶናልድ ትራምፕ የፍርሀት፣ እና ስም የማጠልሸት፣ ዘረኛ፣ የውጭ ዜጎችን የሚፈራ፣ ሴቶችን የሚጠላ እና ውሸታም ቀጣፊ ስሜታዊ አምባገነናዊነት ለአሜሪካ እርባና ቢስ እና ደደብ ፕሬዚዳንትነት መንከን ከሰጡት ማስጠንቀቂያ ጋር አንድ ሆኖ ይገኛል።

ሆኖም ግን ትራምፕ አደገኛ የሆነ ስሜታዊ አምባገነን ነው። ዘረኝነቱን በፓርቲው ውስጥ ለብሶታል። ሆኖም ግን በዋናነት አዲሱን የፋሽስት ባህሪ የተላበሰ ኒዮ ፋሽስት ነው። በቀውስ ውስጥ ስላለች አሜሪካ እና በወንጀል፣ በኃይል እና በድህነት የወደቀች ሀገር እያለ ይናገራል። በአሁኑ ጊዜ አሜሪካ በምጻት ቀን ውስጥ እንደሆነች አድርጎ ለማሳየት በመሞከር ህዝቡን ለማሳመን ይፈልጋል።

ትራምፕ አሜሪካ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንደተዋረደች አድርጎ በማቅረብ የኒዮ ፋሽስት ፕርፓጋንዳ በመዝራት፣ አሜሪካ ሀያል ሀገር እንደሆች እና ዓለምን በኃይል እንደምታንበረክክ በመግለጽ በዘር፣ በጎሳ አናሳነት እና በስደተኞች እና በሕገ መንግስቱ ላይ ያለውን ንቀት በመግለጽ በኃይል ማስተካከል እንደሚችል አድርጎ በመናገር ቃል ይገባል። ትራምፕ የዘር፣ የጎሳ እና የኃይማኖት ጥላቻን በፖለቲካ ቅስቀሳ ዘመቻው እና ፐሮግራሙ ውስጥ በማስገባት ወደ ፕሬዚዳንትነት መሰላል ጫፍ ለመውጣት ይፈልጋል።

በምጻት ለተያዘቸው አሜሪካ የትራምፕ የመፍትሄ ሀሳብ እንዲህ የሚል አዋጅ እና ቃልኪዳን ማወጅ ነው፡ “ለሁሉም አሜሪካውያን በዛሬው ምሽት በሁለም ታላላቅ እና ታናናሽ ከተማዎቻችን፡ አሜሪካንን እንደገና ጠንካራ እናደርጋታለን። አሜሪካንን እንደገና እንድትኮራ እናደርጋታለን። አሜሪካንን እንደገና ሰላም የሰፈነባት እናደርጋታለን። እናም አሜሪካንን እንደገና ታላቅ እናደርጋታለን!“ ነበር ያለው።

የእርሱን የኒዮ ፈሽስት ዘመቻ ለማራመድ የናዚው ጆሴፍ ጎቤል በደብዳው የገለጸውን እና እንዲህ የሚለውን መልዕክት ይከተላል፡

“ውሸት የምትዋሽ ከሆነ እና ይህንንም ውሸት የምተደጋግመው ከሆነ ህዝቡ ቀስ በቀስ ወደ ማመን ይመጣል። ይህ ውሸት ሊቆይ የሚችለው መንግስት ህዝቡን ከፖለቲካ፣ ኢከኖሚ እና/ወይም ወታደራዊ ውሸት እንደ ጋሻ ሆኖ እስከጠበቀው ድረስ ነው። እውነት የውሸት የሞራል ልዕልና ጠላት ስለሆነ መንግስት ሁሉንም ሰላማዊ አመጾች ለመቆጣጠር ኃይልን ይጠቀማል። እውነት የመንግስት ታላቁ ጠላት ነው“ ነበር ያለው።

በአሁኑ ጊዜ ታላቁ ጥያቄ ሆኖ የሚቀርበው ትክክለኛው ደደብ እ.ኤ.አ በ2016 የኋይት ሀውስን ሊቆጣጠር ይችላል ወይ የሚለው ነው።

በአሁኑ ጊዜ ታላቁ ጥያቄ ሆኖ የሚቀርበው የ229 ዓመታት ዕድሜ ያለው ሕገ መንግስት በአዲሶቹ የኒዮ ፋሽስት ደደቦች ድንፋታ የኋት ሀውስን ለመቆጣጠር በሚያደርጉት ሽኩቻ ሊፈርስ ይችላልን የሚለው ነው።

መንከን ለዚህ እንዲህ የሚል የተዘጋጀ መልስ አላቸው፡

“እኔ እስከማውቀው ድረስ እና በምርምርም ለበርካታ ዓመታት እዳረጋገጥኩት እና እንደመዘገብኩት እንዲሁም እኔን እንዲያግዙኝ ከቀጠርኳቸው ሰዎች እስከምገነዘበው ድረስ ከሆነ በዓለም ላይ እስከ አሁን ድረስ የብዙሀኑን ህዝብ ግንዛቤ በመናቅ ገንዘቡን የከሰረ የለም። እንደዚሁም ሁሉ ማንም ቢሆን ቢሮውን ያጣ የለም“ ነበር ያሉት።

በሌላ አገላለጽ እስከ አሁን ድረስ የአሜሪካንን ህዝብ የመረዳት ግንዛቤ በመናቅ የከሰር ሰው ምንም የለም።

መንከን እንዲህ በማለት ገልጸው ነበር፣ “ሁልጊዜ የሚፈጸመው ስህተት በሌላ መንገድ ይሄዳል። ምክንያቱም ብዙሀኑ ህዝብ የመናገር እና የመገንዘብ ከዚህም በላይ በበርካታ ጉዳዮች ማንበብ እና መጻፍ የሚችል ስለሆነ በጭንቅላታቸው ውስጥ ሀሳብ አለ፣ እናም የበለጠ ፍላጎት አላቸው። ይህ ታሳቢ ኢምክንያታዊ ነው“ ነበር ያሉት።

የአሜሪካንን ህዝብ ከትራምፕ ኢምክንያታዊነት ሊጠብቀው የሚችል ማን ነው?

ሂላሪ ክሊንተን፣ በእርግጥ!

ታላቁን እና የመጨረሻዋን የሰብአዊነት ተስፋ ከትራምፓውያን አደጋ እንጠብቅ!

[1] የ”ውሻ ፊሽካ ፖለቲካ” መልዕክት ለጠቅላላው ህዝብ አንድ ነገር የሚል በሚስጥር የተያዘ ቋንቋን ያካትታል። ሆኖም ግን ዒላማ ለተደረገ የህብረተሰብ ክፍል በተጨማሪ ልዩ የሆነ ወይም ደግሞ ውስን የሆነ ትርጉም ይኖረዋል።

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!

ሐምሌ 20 ቀን 2008 ዓ.ም.

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ