21 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ተያዙ
በሐሰተኛ ሰነድና በቱሪስት ስም የገቡ ተሽከርካሪዎች
በሐሰተኛ ሰነድና በቱሪስት ስም የገቡ ተሽከርካሪዎች፣ 7,362 የመትረየስ፣ የክላሽና የቱርክ ሽጉጥ ጥይቶች ይገኙበታል
ኢዛ (ማክሰኞ ሚያዝያ ፲፫ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. April 21, 2020)፦ በአንድ ሳምንት ውስጥ ከ21 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ ዕቃዎችን መያዙን የገቢዎች ሚኒስቴር አስታወቀ። በሐሰተኛ ሰነድና በቱሪስት ስም የገቡ ተሽከርካሪዎች፣ 7,362 የመትረየስ፣ የክላሽና የቱርክ ሽጉጥ ጥይቶች ይገኙበታል።
ሚኒስትሩ ዛሬ ሚያዝያ 13 ቀን እንዳስታወቀው ከሚያዝያ 5 - 12 ባሉት ቀናት በቁጥጥር ሥር ያዋላቸው የኮንትሮባንድ ዕቃዎች የተያዙት የቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያን ጨምሮ እንደ አዳማ፣ ባህርዳር፣ ጅጅጋ፣ ድሬዳዋና ሐረር፣ ሁመራ ጋላፊና የመሳሰሉት የጉምሩክ ኬላዎች ላይ ነው።
ከተያዙት ሕገ-ወጥ የገቢና ወጪ ዕቃዎች ውስጥም በሐሰተኛ ሰነድና በቱሪስት ስም የገቡ ተሽከርካሪዎች፣ የተሽከርካሪዎች መለዋወጫ ዕቃዎች፣ የአዋቂዎችና ሕፃናት አልባሳት፣ ሲጋራ፣ የተለያየ ዐይነት የወርቅ መፈለጊያ ማሽነሪዎች፣ ሁለት የትራክተር መሪ፣ 7,362 የመትረየስ፣ የክላሽና የቱርክ ሽጉጥ ጥይቶች እንዲሁም ድንገተኛ ፍተሻ ተደርጎ በገቢ ዕቃ አወጣጥ ታክስ ሳይከፈል ሊጭበረበር የነበሩ የተለያዩ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ናቸው።
የኮንትሮባንድና ሕገ-ወጥ ንግድን ለመከላከል በሚያጋጥማቸው ተግዳሮቶች ሳይበገሩ ይህን መልካም ሥራ እየሠሩ ያሉ የፀረ ኮንትሮባንድ ግብረ-ኃይል በጋራ በመኾን ሲሆን፤ በዚህ ፈታኝ ጊዜ ራሳቸውን መሥዋዕት በማድረግ ቀንና ሌሊት በፀሐይና ዝናብ እንዲሁም በኮንትሮባንዲስቶች ዛቻ ሳይበገሩ በሠሩት አስደናቂ ሥራ የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹ በቁጥጥር ሥር እንዲውል አድርጓል። (ኢዛ)



