ስለምርጫ የቀረቡ አማራጮች ላይ ለመወሰን ነገ ልዩ ስብሰባ ይደረጋል
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነገ (ማክሰኞ ሚያዝያ 27 ቀን 2012 ዓ.ም.) ከቀረቡት አራት የመፍትሔ አማራጮች ላይ የሕግ፣ የፍትሕና የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርምሮ በሚያቀርበው የውሳኔ ሐሳብ ላይ ተወያይቶ ያጸድቃል
በአራቱ የምርጫ የመፍትሔ ሐሳቦች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ይሰጣል
ኢዛ (ሰኞ ሚያዝያ ፳፮ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. May 4, 2020)፦ ከሰሞኑ እያነጋገረ ባለው የምርጫ መራዘምና ምርጫውን ለማራዘም በቀረቡ አማራጮች ላይ ለመወሰንና የተለያዩ ውሳኔዎችን ለማሳለፍ፤ ነገ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ልዩ ስብሰባ ሊያደርግ ነው።
በምክር ቤቱ ማኅበራዊ ገጽ ላይ ይፋ የኾነው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በነገው (ማክሰኞ ሚያዝያ 27 ቀን 2012 ዓ.ም.) ስብሰባ አገራዊ ምርጫውን በተመለከተ ከቀረቡት አራት የመፍትሔ አማራጮች ላይ የሕግ፣ የፍትሕና የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርምሮ በሚያቀርበው የውሳኔ ሐሳብ ላይ ተወያይቶ ያጸድቃል።
ከዚህም ሌላ ስድስት የብድር ስምምነቶችንም ያጸድቃል ተብሏል። ምርጫ 2012 በኮሮና ቫይረስ ምክንያት በታቀደለት ሰሌዳ መሠረት መካሔድ እንደማይችል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መውሰኑ አይዘነጋም። (ኢዛ)



