Bereket Simon and Tadese Kassa

በምዝበራ ተጠርጥረው ክስ የተመሰረተባቸውና ጥፋተኛ የተባሉት አቶ ታደሰ ካሣ (ግራ) እና አቶ በረከት ስምኦን (ቀኝ)

ፍርድ ቤቱ በዛሬው ችሎት የተከሳሾችን የቅጣት ማቅለያና የዓቃቤ ሕግን የቅጣት ማክበጃ አድምጧል

ኢዛ (ረቡዕ ሚያዝያ ፳፰ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. May 6, 2020)፦ በእነአቶ በረከት ስምኦን የክስ መዝገብ የጥፋተኝነት ውሳኔ ያስተላለፈው የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፤ ዛሬ ረቡዕ ሚያዝያ 28 ቀን ከእነአቶ በረከትና ከዓቃቤ ሕግ የቅጣት አስተያየት ካዳመጠ በኋላ፤ የቅጣት ውሳኔ ለማስተላለፍ ለዓርብ ሚያዝያ 30 ቀን 2012 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጠ።

ፍርድ ቤቱ ባለፈው ሰኞ ሚያዝያ 26 ቀን 2012 ዓ.ም. በዋለው ችሎት በእነአቶ በረከት መዝገብ የተከሰሱትን አቶ በረከት ስምኦን እና አቶ ታደሰ ካሣ የጥረት ኮርፖሬትን ጥቅም በሚጎዳ መልኩ የሥራ ውሎችን ፈጽመዋል በሚል ወንጀል የጥፋተኝነት ውሳኔ መወሰኑን መዘገባችን አይዘነጋም።

አቶ በረከት እና አቶ ታደሰ ከተከሰሱባቸው አራት ክሶች ውስጥ በአንደኛና በሁለተኛ ከሶቹ ጥፋተኛ ሲባሉ፤ በሦስተኛው ክስ ግን ነፃ ኾነዋል። አቶ በረከት ከአራተኛውም ክስ ነፃ መኾናቸው ታውቋል። በዚህ መዝገብ ተከሰው የነበሩት አቶ ዳንኤል ግዛው ከቀረቡባቸው ክሶች በሙሉ ነፃ ተብለዋል።

ፍርድ ቤቱ በዛሬው ችሎት የተከሳሾችን የቅጣት ማቅለያና የዓቃቤ ሕግን የቅጣት ማክበጃ አድምጧል። ተከሳሾች ሕመምተኞችና የቤተሰብ አባል መኾናቸው፤ በፖለቲካና በመንግሥት ሥራ ለረዥም ዓመታት ማገልገላቸውንና ከዚህ በፊት ምንም ዐይነት ወንጀል አለመፈጸማቸውን በጠቃቸው በኩል ለቅጣት ማቅለያነት ማቅረባቸው ታውቋል።

የቅጣት ማክበጃውን ያቀረበው ዓቃቤ ሕግ በበኩሉ፤ በመንግሥትና በፖለቲካ ሥራ በማገልገላቸው ሕጉን ከመደበኛው ሰው በበለጠ እንዲያውቁ የሚያደርግ መኾኑን ገልጿል። ለጥፋተኝነታቸው በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ድንጋጌ 703/1 “ሀ” እና “ለ” ሊቀጡ እንደሚገባ ለፍርድ ቤቱ የቅጣት ማክበጃውን ማቅረቡ ታውቋል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ