አብሮነት

የ“አብሮነት ለኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት” መስራቾች

የሽግግር መንግሥቱ የማይቋቋም መኾኑ አደጋ አለው በማለት መግለጫ አውጥቷል

ኢዛ (እሁድ ግንቦት ፱ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. May 17, 2020)፦ ሦስት ፓርቲዎችን በአባልነት የያዘው አብሮነት ለኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት የሽግግር መንግሥት ጥያቄ ቋሚ የትግል አጀንዳችን ኾኗል በማለት ዛሬ እሁድ ግንቦት 9 ቀን 2012 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

በአቶ ልደቱ አያሌው የሚመራው የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ)፣ ሕብር የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ሕብር ኢትዮጵያ) እና የኢትዮጵያ አገር አቀፍ ንቅናቄ (ኢአን) የመሠረቱት አብሮነት ኢትዮጵያ፤ ዛሬ ባወጣው መግለጫ የሽግግር መንግሥት ምሥረታ በሚለው ሐሳቡ የሚገፋበት ጉዳይ ስለመኾኑ በድጋሚ ያስታወቀበት ኾኗል።

ባለፉት ሁለት ዓመታት በአገሪቱ የተፈጠረውን “የለውጥ ሒደት” የከሸፈ ነው በማለት የሚጀመረው የአብሮነት መግለጫ፤ መሠረታዊ የአገሪቱን የፖለቲካ ችግሮች ለመፍታት በሚያስችል አግባብ ያልተካሔደና የከሸፈ መኾኑን እንደሚገነዘብ አስታውቋል።

ይህም በመኾኑ አገሪቱን ወደ አንድ አዲስና ጤናማ የሽግግር ሒደት የሚያስገባ አማራጭ ሐሳብ በረቂቅ ደረጃ አዘጋጅቶ ለሕዝብ ውይይት አቅርቦ እንደነበር የሚያትተው መግለጫ፤ አሁን በሥልጣን ላይ ያለው የብልጽግና ፓርቲ ቃሉን ጠብቆ ኢትዮጵያን ወደ መዋቅራዊ ዴሞክራሲ ማሸጋገር አለመቻሉንም ጠቅሷል። አሁን በአገሪቱ ያሉት የፖለቲካ ችግሮችም የተፈጠሩት ይጠበቅ የነበረው ለውጥ ካለመምጣቱ ጋር የተያያዘ እንደኾነም አመልክቷል።

ይህም በመኾኑ ምርጫ ሳይሆን፤ ለሁለት ዓመት የሚቆይ ሁሉ አቀፍ የኾነ የእርቅና የአንድነት የሽግግር መንግሥት መቋቋም አለበት ብሎ በጽኑ እንደሚያምን በዛሬው የፓርቲው መግለጫ ገልጿል።

ብልጽግና ባለፉት 29 ዓመታት እንደኾነው ሁሉ አሁንም “የአገሪቱ ዕጣ ፈንታ መወሰን የሚገባኝ እኔ ብቻ ነኝ” በሚል መታበይ ወይም፤ “እኔ አሻግራችኋለሁ” በሚል ያልተገባ ፍልስፍና በሥልጣን ላይ የሚቀጥል ከኾነ፤ አገሪቱ በከፍተኛ ፍጥነት ወደ አደገኛ የብጥብጥ አዙሪት ልትገባ ትችላለችም በማለት አብሮነት አመልክቷል። የመግለጫውን ሙሉ ቃል አስነብበኝ! (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!