ትግራይ ክልል፣ መቀሌ

ትግራይ ክልል፣ መቀሌ

ፌዴራል ይግባ የሚል ጥያቄ እየተነሳ ነው

ኢዛ (ሰኞ ግንቦት ፲፯ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. May 25, 2020)፦ በትግራይ ክልል በሚገኙ ከተሞች ድምፆች ጎልተው እየተሰሙ ሲሆን፤ የፌዴራል መንግሥት ጣልቃ ይግባልን ጥያቄዎች እየተሰሙ ነው።

በክልሉ ተቃውሞ የተቀሰቀሰባቸው አካባቢዎች ነዋሪዎች አደባባይ ጭምር ተቃውሟቸውን ማሰማት ከጀመሩ ድፍን አንድ ሳምንት የኾናቸው ሲሆን፤ በትናንትናው ዕለት (እሁድ ግንቦት 16 ቀን 2012 ዓ.ም.) ግን ለየት ባለመልኩ ተቃውሞው ተካሒዷል።

በክልሉ የተፈጠረውን ተቃውሞ ጎልቶ እንዲታይ ያደረገው ደግሞ “ፈንቅል” በሚል መጠሪያ የተቃውሞ እንቅስቃሴው እንዲካሔድ ጥሪ መደረጉ ነው።

ከሰሞኑ ጉዳዩን በተመለከተ በተከታታይ ከምስል ጭምር የተደገፉ መረጃዎች እንደሚያሳዩት በሽሬ፣ አክሱም፣ ደደቢት፣ ናእዲር፣ መቀሌ፣ ጨር ጨር፣ ሐዋነ፣ ወጀራት የዕዳጋ ሕብረት፣ … አካባቢዎች የተለያየ መልእክትና ጥያቄዎችን ይዘው ነዋሪዎች አደባባይ ወጥተው ተቃውሞዋቸውን አሰምተዋል።

በትግራይ ክልል ከዚህ ቀደም ባልታየ ሁኔታ እየሰፋ ያለው የተቃውሞ ድምፅን ተከትሎ በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችም ይህንን ተቃውሞ በተመለከተ እያሰፈሩዋቸው ያሉት መረጃዎች በየአካባቢው የተነሳው ተቃውሞ በተለያዩ ከተሞች እየሰፋ መኾኑን ነው።

ሕወሓት ትግል የጀመረበት ደደቢት ሳይቀር ሕወሓትን የሚቃወም ትእይንት መካሔዱን የሚጠቁሙት መረጃዎች ያሳያሉ።

በሽሬ፣ ማይሐንስ፣ ደደቢት፣ ሂዋነ እና በሌሎች ከተሞች እየተሰማ ያለው ተቃውሞ የቀጠለ ሲሆን፣ በአንዳንድ አካባቢዎችም መንገድ በመዝጋት ጭምር የተካሔደ ነው።

ትናንትናና ከትናንት ወዲያ ተቃውሞ ከተካሔደባቸው ከተሞች አንድዋ የኾነችው አክሱም ከተማ ተጠቃሽ ኾናለች። የከተማውን አውራ ጎዳና በመዝጋትና ጎማ በማቃጠል ጭምር ወጣቶች ተቃውሞዋቸውን ገልጸዋል ተብሏል። ከገለልተኛ አካል ማረጋገጫ ባይገኝም አንድ ወጣት ከአንድ የትግራይ ልዩ ኃይል መሣሪያ ነጥቆ የልዩ ኃይል አባላትን አቁስሏል።

የአክሱም ተጎራባች ነች የተባለችው የናእዴር ከተማ የቀድሞ ወረዳችን ይመለስ የሚል ጥያቄ ይዘው ለስብሰባ ተቀምጠዋል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ችላ በማለት የተካሔደው ይህ ስብሰባ፤ ነዋሪዎች በብዛት ወጥተው የተሳተፉበት ነበር።

ከትናንት በስቲያ የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ነብዩ ስሑል ሚካኤል፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥያቄ፣ ፍላጎትና መፃኢ እድል ተመሳሳይ ነው የምንለው በምክንያት ነው በሚል ርዕስ ባሰፈሩት ጽሑፍ፤ የሕወሓት ትጥቅ ትግል የተጀመረበት ማይሐንስ፣ ደደቢትም ሳይቀር ሰባት ቀን ያስቆጠረ የሕዝብ እንቢተኝነት እየተካሔደ ይገኛል በማለት፤ በትግራይ ክልል እየተካሔዱ ስላሉ ተቃውሞዎች ገልጸዋል። አያይዘውም በዚህ ሕዝባዊ እምቢተኝነት፤ እናቶችና አዛውንቶች ሳይቀሩ እየተሳተፉበት የሚገኙ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ በሰፊው እንደታየው ስር የሰደዱና ሕዝብን ከመጠን በላይ ያማረሩ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በማንገብ መንገድ በመዝጋትና ሰላማዊ ሰልፍ በማካሔድ ተቃውሟቸውን እየተገለጹ ይገኛል በማለት አክለዋል።

የክልሉ መንግሥት የጥቅሙና የአፈናው መረብ በመዘርጋት በመቀሌና በመቀሌ ዙሪያ ብቻ ተወስኖ መልስ መስጠት ወይም እንቢተኝነቱን ማስቆም አቅቶት መላ ያጣ ኾኖ ተስፋ የቆረጠ ተመልካች ኾኗል በማለት ገልጸዋል።

ትናንት ማምሻውን ኢቢሲ በስልክ ያነጋገራቸው የሽሬ ከተማና የሌሎች አካባቢ ነዋሪዎች፤ በትግራይ የጸጥታ ችግር መከሰቱን በማመልከት፤ የፌዴራል መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ እስከመጠየቅ ደርሰዋል። በጉዳዩ ላይ የክልሉን ኮምዩኒኬሽን ቢሮ ለማነጋገር የተደረገው ሙከራ እንዳልተሳካለትም ዘገባው አመልክቷል።

ኢቢሲ ካነጋገራቸው የክልሉ ነዋሪዎች በሕወሓት አገዛዝ ዜጎች ሲበደሉ መቆየታቸውና ተጠቃሚ ኾነው የቆዩት በሥልጣን ያሉት መኾናቸውን በመጠቆም፤ የሕወሓትና የክልሉን ፍላጎት ለይቶ ማየት ያስፈልጋል ብለዋል። ወጣቶች እየተጎዱ በመኾኑና ጠቅላይ ሚኒስትሩም የእነዚህን ወጣቶች ጉዳይ ይመልከት በማለት ጥሪያቸውን ያስተላለፉ ሲሆን፣ የክልሉም ጉዳይ ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቀዋል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!