በኢትዮጵያ በአንድ ቀን የተያዙ ሰዎች ወደ 137 አሻቀበ
የጤና ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ጤና ኢንስቲትዩት
በኮሮና የሞተ ሰው ስምንት ደረሰ
109ኙ ከአዲስ አበባ ናቸው
ኢዛ (ዓርብ ግንቦት ፳፩ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. May 29, 2020)፦ ከዕለት ዕለት እየጨመረ የመጣው የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ቁጥር አሳሳቢ እየኾነ በመጣበት በዚህ ወቅት በ24 ሰዓት ውስጥ በተደረገ ምርመራ 137 ሰዎች መያዛቸውና የአንድ ሰው ሕይወት ማለፉ ተገለጸ።
በዛሬ (ዓርብ ግንቦት 21 ቀን 2012 ዓ.ም.) የጤና ሚኒስቴር መረጃ 137 የሚኾኑ በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች የተገኙት 5,015 የሚኾኑ ሰዎች ምርመራ ተደርጎላቸው ነው። ይህም በኢትዮጵያ የቫይረሱ ተጠቂዎችን ቁጥር ወደ 968 አድርሶታል።
የዛሬውን መረጃ አስደንጋጭ የሚያደርገው ከ137ቱ ተጠቂዎች ውስጥ 109 የሚኾኑት የውጭ የጉዞ ታሪክ የሌላቸውን በቫይረሱ ከተያዘ ሰው ጋር የታወቀ ግንኙነት የሌላቸው መኾኑን ነው። 20ዎቹ የውጭ የጉዞ ታሪክ ያላቸው ሲሆን፣ ስምንቱ በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር የታወቀ ግንኙነት ያላቸው ናቸው። እነዚህ ተጠቂዎች ከ4 - 75 የዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ናቸው። ከ137ቱ ተጠቂዎች 109ኙ ከአዲስ አበባ፣ 17ቱ ከአማራ ክልል፣ ስምንቱ ከኦሮሚያ፣ ሁለቱ ከቤንሻንጉልና አንደ ከአፋር የተገኙ ናቸው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በቫይረሱ ተጠቅተው የሞቱት ሰዎች ቁጥር በዛሬው ዕለት ስምንት መድረሱ ታውቋል። ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ መሞታቸው የተገለጹት የ62 ዓመት ጎልማሳ ናቸው። ጎልማሳው የኮሮና ምርመራ ውጤቱ ከመታወቁ በፊት ማረፋቸውም ታውቋል።
በኢትዮጵያ ምርመራ የተደረገላቸው ሰዎች ቁጥር 100 ሺህ ተሻግሮ፤ 101,581 ደርሷል። ስድስት ያገገሙ ሰዎች መገኘታቸው፤ ያገገሙትን ሰዎች ቁጥር 197 አድርሶታል። በሕክምና ላይ ያሉ ደግሞ 761 መኾናቸው ታውቋል። በጽኑ የታመሙ ሰዎች ደግሞ አራት መድረሱ ተመልክቷል። (ኢዛ)



