ሕወሓት፣ ኮሮና እና ምርጫ ቦርድ

“በትግራይ ምርጫ አላስፈጽምም” የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ለትግራይ ክልል ምክርቤት የሰጠው ምላሽ

ቦርዱ ከትግራይ ክልል ምክር ቤት የተጠየቀውን የሰው ኃይል፣ የሎጄስቲክስ እና የቁሳቁስ አቅርቦት የሚሰጥበት የሕግ አግባብ አለመኖሩንም አሳውቋል

ኢዛ (ረቡዕ ሰኔ ፲፯ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. June 24, 2020)፦ የትግራይ ክልል ምክር ቤት በክልሉ ምርጫን ለማካሔድ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያቀረበውን ጥያቄ ቦርዱ ውድቅ አደረገው። ቦርዱ ከትግራይ ክልል ምክር ቤት የተጠየቀውን የሰው ኃይል፣ የሎጄስቲክስ እና የቁሳቁስ አቅርቦት የሚሰጥበት የሕግ አግባብ አለመኖሩንም አሳውቋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከትግራይ ክልል 6ኛውን ዙር የክልል ምክር ቤት ምርጫ እንዲፈጸምለት ያቀረበውን ጥያቄ በማስመልከት ባወጣው መግለጫ፤ የትግራይ ክልል ያቀረበውን ጥያቄ ውድቅ ከማድረጉም በላይ፤ ጥያቄውን ሕጋዊ አግባብ የሌለው መኾኑንም ያሳወቀበት ነው። የመግለጫው ሙሉ ቃል የሚከተለው ነው። (ኢዛ)

የትግራይ ክልል ምክር ቤት የክልል ምክር ቤት ምርጫ እንዲፈጸምለት ለቦርዱ ያቀረበውን ጥያቄ አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተሰጠ መግለጫ

የትግራይ ክልል ምክር ቤት “ኮቪድ 19ኝን እየተከላከለ 6ኛውን ዙር ምርጫ ለማካሔድ የወሰነ በመኾኑ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት በሚያዘው መሰረት ቦርዱ ውሳኔውን ተቀብሎ ምርጫውን እንዲያስፈጽም፣ ምርጫውን ለማካሔድ የሚያስፈልግ የሰው ኃይልና ሎጂስቲክስ ዝግጅት እንዲያደርግ እና ውሳኔውን ለምክር ቤቱ እንዲያሳውቀን” ሲል ጥያቄ አቅርቧል።

በመላ አገሪቱ በፌዴራልም ኾነ በክልሎች የሚደረጉ ምርጫዎችን የማስፈጸም ሥልጣን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መኾኑ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ መንግሥት አንቀፅ 102 (1) ላይ ተደንግጓል። ሕገ መንግሥቱን መሰረት አድርጎ የቦርዱን ሥልጣን እና ኃላፊነት የወሰነው የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1133/2011 በአንቀጽ 7.1 ይህ የቦርዱ ሥልጣን በአገሪቱ ውስጥ የሚፈጸሙ ምርጫዎች እና ሕዝበ ውሳኔዎችን በሙሉ እንደሚሸፍን በተብራራ ሁኔታ ገልጾታል።

በተጨማሪም የቦርዱን የሥራ ኃላፊነቶች በተለያየ ሁኔታ በዝርዝር በሚገዙት ሕጎች ማለትም በአዋጅ ቁጥር 1133/2011 እና በአዋጅ ቁጥር 1162/2011 እንደተደነገገው በማንኛውም የምርጫ ዑደት የሚፈጸሙ ዋና ዋና ክንዋኔዎች ማለትም የምርጫ ጊዜ ሰሌዳን ማውጣት፣ ለምርጫ የሚወዳደሩ የፖለቲካ ፓርቲዎችን መመዝገብ፣ መቆጣጠር እና ማስተዳደር፣ የምርጫ አስፈፃሚዎችን መልምሎ ማሰማራት፣ ጣቢያዎችን ማቋቋም፣ ምርጫውን ከተጽእኖ ነፃ እና ፍትሐዊ በኾነ መልኩ ማስፈጸም፤ በመጨረሻም የውድድሩን ውጤት አረጋግጦ ለሕዝብ ይፋ ማድረግ እና የመሳሰሉት ከማንኛውም የመንግሥት ተቋም በተለየ ለቦርዱ የተሰጠ እና ከማንም አካል ጋር የማይጋራው ሕጋዊ ሥልጣኑ ነው።

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫን ለማስፈፀም የሚያስፈልጉ እንቅስቃሴዎችን በማከናወን ላይ እያለ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ባገራችንም በመከሰቱ ምርጫውን ለማስፈፀም ሲያካሒዳቸው የነበሩት ሥራዎች እንደተስተጓጎሉ ይታወቃል። ወረርሽኙ በኢትዮጵያ መከሰቱ እንደተረጋገጠ ኹናቴውን መገምገም አስፈላጊ ኾኖ በመገኘቱ ቦርዱ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር ካደረገ በኋላ 6ኛውን አገራዊ ጠቅላላ ምርጫ ቀደም ሲል ቦርዱ ባወጣው የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ማካሔድ የማይቻል በመኾኑን ወስኖ ይህንኑ ውሳኔ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቧል። ምክር ቤቱም የቀረበለትን የቦርዱን ውሳኔ ተቀብሎ የሕገ መንግሥት ትርጉም እንዲሰጥበት መወሰኑ ይታወሳል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሰኔ 3 ቀን 2012 ዓ.ም በሰጠው ውሳኔ ምርጫውን የኮቪድ 19 ወረርሽኝ የሕዝብ ጤና ሥጋት ኾኖ ባለበት ሁኔታ ማካሔድ የማይቻል በመኾኑ፤ የፌደራልና ክልል ምክርቤቶች የሥልጣን ዘመን እንዲቀጥል፤ እንዲሁም አጠቃላይ ምርጫው ሥልጣን ያላቸው አካላት ወረርሽኙ የሕዝብ ጤና ሥጋት አለመኾኑን ካረጋገጡበት ጀምሮ ከዘጠኝ ወር እስከ አንድ ዓመት ባለው ጊዜ እንዲካሔድ ወስኗል።

ስለሆነም፤

1. 6ኛው አገራዊ ጠቅላላ ምርጫ የሚካሔድበት ጊዜ እንዲራዘም ምክንያት የኾነው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ሁኔታ እንደገና ተገምግሞ ምርጫ ማካሔድ የሚያስችል ሁኔታ መፈጠሩ እስኪረጋገጥ ድረስ፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በየትኛውም የአገሪቱ ክልል ምርጫ አያካሒድም።

2. በተጨማሪም ከላይ እንደተገለጸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የፖለቲካ ፓርቲዎችን መመዝገብ፣ መቆጣጠር እና ማስተዳደር፣ የምርጫ ጊዜ ሰሌዳን ማውጣት፣ የምርጫውን ከተጽእኖ ነፃ እና ፍትሐዊ በኾነ መልኩ ማስፈጸም ሥልጣን ያለው ብቸኛ ተቋም ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ ምርጫ የጊዜ ሰሌዳን፣ አፈጻጸምንም ሆነ ተያያዥ ሁኔታን የሚወስነውም ቦርዱ ብቻ ነው። በመኾኑም የትግራይ ክልል ምክር ቤት በክልሉ ውስጥ 6ተኛውን ዙር የክልል ምክር ቤት ምርጫ እንዲካሔድ ውሳኔ ለመስጠት፤ እንዲሁም ቦርዱ ይህንን ውሳኔውን ተቀብሎ ሊያስፈጽም ይገባል የሚልበት ሕጋዊ መሠረት የለውም።

በመኾኑም ቦርዱ ከላይ በተዘረዘሩት ምክንያቶች የትግራይ ክልል ምክር ቤት የክልል ምክር ቤት ምርጫን አስመልክቶ የሰጠውን ውሳኔ እንዲያውቅለትም ኾነ፤ ምርጫ እንዲያስፈፅምለት ያቀረበውን ጥያቄ ያልተቀበለው መኾኑን፣ የተጠየቀውን የሰው ኃይል፣ የሎጄስቲክስ እና የቁሳቁስ አቅርቦት የሚሰጥበት የሕግ አግባብ አለመኖሩን ያሳውቃል። 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ