የአምስት የእርቀ ሰላም ኮምሽን አባላት ሹመት ጸደቀ
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት
ተሿሚዎቹ ቃለ መሃላ ፈጽመዋል
ኢዛ (ዓርብ ሰኔ ፲፱ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. June 26, 2020)፦ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ትናንት ሐሙስ ሰኔ 18 ቀን 2012 ዓ.ም ባካሔደው ስብሰባው የተጓደሉ የእርቀ ሰላም ኮሚሽን አባላት ሹመትን የተመለከተ ሲሆን፣ በዚህም በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ የቀረቡለትን የተጓደሉ የእርቀ ሰላም ኮሚሽን አባላትን ለማሟላት አምስት አበላቶችን ሹመት አጽድቋል።
ለኮሚሽኑ አባልነት ምክር ቤት ሹመታቸውን ያጸደቀላቸው ሬቭናንድ ደረጀ ጀምበሩ፣ አቶ ደመላሽ ያደቴ፣ ዶክተር እዝራ አባተ፣ ወይዘሮ ፋጡማ ሀሴ እና ጋራድ ኩልሜ መሐመድ ናቸው።
በተጓደሉ የእርቀ ሰላም ኮምሽን አባላት ኾነው ሹመታቸው የጸደቀላቸው አምስቱ የእርቀ ሰላም ኮሚሽን አባላትም፤ በምክር ቤቱ ፊት ቀርበው ቃለ መሃላ ፈጽመዋል። ምክር ቤቱ ከዚህ ሹመት ማጽደቅ ሌላ የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የአፍሪካ ሕብረት ሰንደቅ ዓላማ፣ መዝሙር እና የአፍሪካ ቀን ረቂቅ አዋጅ በተመለከተ ያቀረበውን ሪፖርትና የውሳኔ ሐሳብ ተመልክቶ ከተወያየ በኋላ፤ የአፍሪካ ሕብረት ሰንደቅ ዓላማ፣ መዝሙር እና የአፍሪካ ቀን አዋጅን አጽድቋል። (ኢዛ)



