የኢህአዴግ መንግሥት አቶ ስዩም መስፍንን ወደ ቻይና ላከ
Ethiopia Zare (ሐሙስ ኅዳር 9 ቀን 2003 ዓ.ም. November 18, 2010)፦ ’መተካካት’ በሚል መርኅ የሥልጣን ለውጥ እንደሚያደርግና በአዳዲስና ወጣት ተሿሚዎች እንደሚተካ ቃል የገባው የኢህአዴግ መንግሥት፤ የቀድሞ ቱባ ቱባ ባለሥልጣናቱን በቋሚ ወይንም በባለሙሉ ሥልጣን አምባሣደርነት መሾሙን ካሳወቀ በኋላ፤ ትናንት አቶ ስዩም መስፍንን ወደ ቤጂንግ እንደሚልክ ይፋ አደረገ።
አቶ ስዩም ከ19 ዓመታት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነታቸው ተነስተው ጠ/ሚኒስትር መለስ በተደጋጋሚ ወዳጅነቷን በማሞጋገስ ከሚገልጿት ቻይና በሙሉ ሥልጣን አምባሣደርነት እንዲያገለግሉ የተሾሙ ሲሆን፤ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ግርማ ብሩ ወደ አሜሪካ መናገሻ ዋሽንግተን ዲሲ እንደሚያመሩ ለማወቅ ተችሏል።
አፈ ጉባዔ የነበሩት አምባሣር ተሾመ ቶጋ በፈረንሣይ፣ ዶ/ር ካሱ ኢላላ ደግሞ በቤልጅየም የመጀመሪያዎቹ ባለ ሙሉ ሥልጣን ተሿሚ አምባሣደሮች ሆነዋል።
ለረጅም ጊዜ የአቶ ስዩም መስፍን ምክትል ሆነው የሠሩት የቀድሞው ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ተቀዳ ዓለሙ በተባበሩት መንግሥታት መልዕክተኛ ሆነው ሲላኩ፤ በየመንና ግብጽ የዐረቡን ማኅበረሰብ ይስባሉ ተብለው የተገመቱት አቶ ሐሰን አብደላ እና አቶ መሐመድ ድሪር በአምባሣደርነት ተሹመዋል።
ሌሎች የሹመት ድልድሎች በአውሮፓና በአፍሪካ ሀገራት የተሰጠ መሆኑ ታውቋል።



