Amhara Prosperity Party and TPLF

የአማራ ብልጽግና ፓርቲና የሕወሓት ፍጥጫ

ምሽግና በክልል ደረጃ የሚያዝ የጦር መሣሪያዎችም ታይተዋል

ኢዛ (ረቡዕ ሐምሌ ፳፱ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. August 5, 2020)፦ ሕወሓት ከአማራ ክልል ጋር በሚዋሰንባቸው ቦታዎች የትንኮሳ እንቅስቃሴ ውስጥ መግባቱ እንደሚታወቅና በክልል ደረጃ ሊያዙ የሚችሉ የጦር መሣሪያዎችን በመያዝ እየተንቀሳቀሰ መኾኑን የአማራ ብልጽግና ፓርቲ አስታወቀ።

የአማራ ብልጽግና ፓርቲ በፌስቡክ ገጹ ላይ “የሕወሓት ቀቢፀ ተስፋ የተጠናወተው የትግል ስልት ለምንና ለማን?” በሚል ርዕስ ባሰፈረው ጽሑፍ፤ ሕወሓት እንደ ወትሮው ሁሉ ለጦርነት ቀርቶ ለአቅመ ኩርፊያ የሚያበቃ ነባራዊ ሁኔታ በሌለበት የሥነ-ምህዳር፤ ፀብ የሚጠማው ድርጅት ነውም ብሎታል።

አያይዘውም በአሁኑ ሰዓት በአማራ ክልል ጋር በሚዋሰንባቸው ሁሉም አካባቢዎች የትንኮሳ እንቅስቃሴ ውስጥ መግባቱ ይታወቃል ብሏል።

ምሽግ በስፋት መቆፈር፣ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የታጠቀ ኃይል ማሰማራት፣ በክልል ደረጃ መያዝ የሌለባቸው የተለያዩ የቡድን መሣሪያዎች የታጠቁ ኃይሎችን በማራራቅ የአካባቢውን ሰላም የማወክ ሥራዎች ሕወሓት እየሠራ መኾኑንም አመልክቷል።

ይኸው የአማራ ብልጽግና ጽሑፍ ጨምሮ እንደሚያመለክተው፤ በእነዚህ የድንበር አካባቢዎች የሕወሓት ነባር አመራሮችና በወንጀል የሚፈለጉ የደኅንነት ሰዎች በአካባቢው አሰማርቶ የቅኝት ሥራ መሥራት፣ በአጠቃላይ ለጦርነት የመዘጋጀት ዝንባሌ በተካረረ መንገድ መስተዋሉንም አመልክቷል።

“የዚህ ሁሉ ዝግጅት ምክንያቱ ተስፋ መቁረጥና ከወደቁበት አዘቅት ለመውጣት የሞት ጣር ትንቅንቅ ነው” በማለት ስለሕወሓት ወቅታዊ ሁኔታ ያሰፈረው ሐተታ ያመለክታል።

የአማራ ብልጽግና ፓርቲ በፌስቡኩ ስለሕወሓት ሰፋ ያለ ማብራሪያ የሰጠ ሲሆን፤ በሌላ ርዕስም ተመሳሳይ ትንተና ያሰፈረበት ነው። የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ለሕወሓት ለየት ባለ ሁኔታ ካሰፈራቸው ጽሑፎች “የሕወሓት ቀቢጸ ተስፋ የተጠናወተው የትግል ስልት ለምንና ለማን?” በሚል ርዕስ ያቀረበውን ጽሑፍ ሙሉውን ለማንበብ እዚህ ይጫኑ! (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!