Ethiopia Zare (እሁድ መስከረም ፳፭-25 ቀን ፳፻፩-2001 ዓ.ም. October 5, 2008)፦ ከስያሜ ጋር በተያያዘ ብጥብጥ በቡታጅራ ከተማ ታስረው የነበሩ 120 እስረኞች ባለፈው ቅዳሜ ተፈቱ።

 

የከተማ ነዋሪዎች ጉዳዩን በሚመለከት፣ በቡታጅራ ከተማ ከመስቃን እና ከዶቢ ስያሜ ጋር በተያያዘ በተነሳው ረብሻ ምክንያት ታስረው ለ50 ቀናት በእስር ከቆዩት 160 ከሚጠጉ እስረኞች መካከል 120 ያህሉ መፈታታቸውንና 37 ሰዎች በእስር ላይ መቅረታቸውን ጠቁመው፣ ረቡዕና ኀሙስ ዕለት በድጋሚ ሰባት ሰዎች መታሰራቸውን ገልጸዋል።

 

ረብሻው የተነሳው 41 ቀበሌ የያዘው መስቃን ወረዳ አንድ ቀበሌ ከያዘው ዶቢ ጋር ተቀላቅሎ “መስቃን ዶቢ” አይባልም በሚል ነዋሪዎች ባነሱት ተቃውሞ ሲሆን፣ አንዳንድ የዶቢ ነዋሪዎች በበኩላቸው ዶቢ አንድ ቀበሌ አለመሆኑንና “መስቃን ዶቢ” የሚለው መጠሪያ ከዐፄ ኃይለሥላሴ ጊዜ ጀምሮ የነበረ መጠሪያ እንደሆነ ይገልፃሉ።

 

በዚህ ስያሜ በተፈጠረ አለመግባባትም ጉዳዩ ወደ ረብሻ ተለውጦ በከተማው የሚገኙ የባለሥልጣን ቤቶች ፈራርሰዋል፣ ለአንድ ሕፃን እጅ መቆረጥ፣ እንዲሁም ለበርካታ የከተማው ነዋሪ ለእስር መዳረግ ምክንያት ሆኗል።

 

ባለፈው ቅዳሜ መስከረም 17 ቀን ወደ 120 የሚሆኑ እስረኞች ሲለቀቁ በከተማው ከፍተኛ ደስታ እንደነበረ ምንጮቻችን ጠቅሰው “ነገር ግን ጉዳዩ ባለሥልጣናቱን እርስ በርስ የከፋፈለ፣ ነዋሪውንም የማያግባባ በመሆኑ እስካሁን መፍትሔ አልተገኘም” ባዮች ናቸው።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ