ወላይታ ዞን ችግር አለ
መምህር አሰፋ ወዳጆ
የዞኑ አመራሮች እየታሰሩ ነው
በተፈጠረው አለመረጋጋት ሰዎች ሞተዋል
ኢዛ (ሰኞ ነኀሴ ፬ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. August 10, 2020)፦ በወላይታ ዞን በተፈጠረው አለመረጋጋትና ግርግር የሰዎች ሕይወት መጥፋቱንና ለችግሩ መንሥኤ ናቸው የተባሉ የዞኑ አመራሮችና ሌሎች እጃቸው አሉባቸው የተባሉ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር እየዋሉ መኾኑ ተሰማ። በቁጥጥር ከዋሉት ሰዎች ውስጥ አቶ አሰፋ ወዳጆ ይገኙበታል።
ከወላይታ የክልል ጥያቄ ጋር በተያያዘ ዛሬ በተፈጠረው አለመረጋጋት በገለልተኛ አካላት ባይረጋገጥም፤ እስካሁን ወደ አስር የሚጠጉ ሰዎች ስለመሞታቸው የተነገረ ሲሆን፤ የመቁሰል አደጋ የደረሰባቸውም እንዳሉ ታውቋል።
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ያለመረጋጋቱ የተፈጠረው የክልል ጥያቄው በሰላማዊ መንገድ እንዳይመለስ በሕዝብና በመንግሥት መካከል ጥርጣሬ እንዲፈጠር፤ እንዲሁም ለውጡን ከማይደግፉ አካላት ጋር እየሠሩ ነው የተባሉ የዞኑ ከፍተኛ አመራሮች በቁጥጥር ሥር እየዋሉ ስለመኾኑ በመገለጹ ነው።
በዚህም ምክንያት በዞኑ በአንዳንድ አካባቢዎች ግርግር የተፈጠረ ሲሆን፤ መንገድ ከመዝጋት ጋር በተደረገ እንቅስቃሴ ተወሰደ በተባለ እርምጃ ለሰዎች መሞትና መቁሰል ምክንያት ኾኗል።
የደቡብ ክልል የሰላምና ጸጥታ ቢሮ መግለጫ ደግሞ በተፈጠረው ኹከት አንድ ሰው ስለተገደሉ አመልክቷል።
የዞኑ ከፍተኛ አመራሮች የታሰሩትም ሕገ ወጥ በኾነ መንገድ አገር ለማፍረስ ከሚንቀሳቀሱ አካላት ጋር በመኾንና አብረው በመሥራት ላይ የነበሩ ስለመኾናቸው ታውቆ፤ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ይኸው የቢሮው መግለጫ ያመለክታል።
የዞኑ አመራሮች መታሰር የጀመሩት ከትናንት (እሁድ ነኀሴ 3 ቀን 2012 ዓ.ም.) ጀምሮ ነው። ኾኖም በሶዶ እና በቦዲቲ ባሉ አንዳንድ አካባቢዎች የተፈጠረውን ኹከት ተከትሎ የመከላከያ ሠራዊቱ እርምጃ እየወሰደ ነው ተብሏል። (ኢዛ)



