23 ሺህ ግራም ወርቅ በቦሌ በኩል ሊወጣ ሲል ተያዘ
ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ የተያዘው 23 ሺህ ግራም ወርቅ
ግምቱ ከ46 ሚሊዮን ብር በላይ ነው
ኢዛ (ቅዳሜ ነኀሴ ፱ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. August 15, 2020)፦ በትናንትና ዕለት ግምቱ ከ46 ሚሊዮን ብር በላይ የሚኾን 23 ሺህ ግራም ወርቅ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ ወደ ዱባይ ሊወጣ ሲል መያዙን የገቢዎች ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ዛሬ ቅዳሜ ነኀሴ 9 ቀን 2012 ዓ.ም. እንዳስታወቀው፤ 23 ሺህ ግራም ወርቁን ከአገር ሊያስወጣ ሲል በቁጥጥር ሥር የዋለው አንድ ናይጄሪያዊ ነው።
ወርቆቹን በሕገወጥ መንገድ ወደ ዱባይ ይዞ ለመውጣት ሲሞክር በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ የተያዘው ናይጄሪያዊ በቁጥጥር ሥር ውሎ ምርመራ እየተደረገበት ነው።
ይህንን ያህል ወርቅ ግለሰቡ ከየት እንዳመጣ መረጃው የጠቀሰው ነገር ባይኖርም፤ በሕገ ወጥ መንገድ ሊወጣ ነበር የተባለውን ወርቅ ለያዙት የጉምሩክ ሠራቶችና የጸጥታ አካላት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ምስጋና አቅርቧል። (ኢዛ)



