Lidetu Ayalew (Photo: Addis Fortune)

አቶ ልደቱ አያሌው (ፎቶ፡ ፎርቹን)

ላቀረቡት የዋስትና ጥያቄ ፍርድ ቤቱ ነገ ውሳኔ ይሰጣል

ኢዛ (ሐሙስ መስከረም ፯ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. September 17, 2020)፦ የዋስትና ጥያቄያቸው ተቀባይነት ያጣውና በእስር ላይ የሚገኙት አቶ ልደቱ አያሌው ያልተፈቀደ የጦር መሣሪያ በመያዝ ወንጀል ክስ ቀረበባቸው።

በምሥራቅ ሸዋ ዞን ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በአቶ ልደቱ ላይ ክሱን የመሠረተው በዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ነው።

በዛሬው (ሐሙስ መስከረም 7 ቀን 2013 ዓ.ም.) የዓቃቤ ሕግ ክስ መሠረት አቶ ልደቱ የጦር መሣሪያ አስተዳደር አዋጅን በመተላለፍ ክሱ የተመሠረተባቸው መኾኑ ታውቋል።

አቶ ልደቱ የአርቲስት ሐጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ ሰኔ 23 እና 24 ቀን 2012 ዓ.ም. በደብረዘይት (ቢሾፍቱ) ከተማ አመጽና ኹከት እንዲቀሰቀሰ በገንዘብ ሲደግፍና ሲያስተባብሩ ነበር ተብለው ምርመራ ሲደረግባቸው እንደነበር ይታወሳል።

ይሁን እንጂ ቀድሞ በተጠረጠሩበት ወንጀል ምርመራ ሲያካሒድ ፍቃድ የሌላቸው የጦር መሣሪያ አግኝቼባቸዋለሁ በማለት ዓቃቤ ሕግ ዛሬ ክስ መሥርቶባቸዋል።

በዓቃቤ የክስ መዝገብ ላይ እንደተጠቀሰው በአቶ ልደቱ የቢሾፍቱ መኖሪያ ቤት ውስጥ አንድ ሽጉጥ ከአንድ ካርታና ከ16 ፍሬ ጥይት ጋር በፍተሻ መገኘቱን ጠቅሷል።

በአቶ ልደቱ በኩል ሕመምተኛ መኾናቸውንና አሁን የተከሰሱበት ክስ ዋስትና የማያስከለክላቸው በመኾኑ፤ እንዲሁም ሕክምናቸውን ለመከታተል የዋስትና ጥያቄ በጠበቆቻቸው በኩል ቀርቧል። ዓቃቤ ሕግ የዋስትና ጥያቄውን ተቃውሟል።

የሁለቱን ወገኖች ክርክር ያደመጠው ፍርድ ቤት የአቶ ልደቱን የዋስትና ጥያቄ ላይ ትእዛዝ ለመስጠት፤ እንዲሁም በክሱ ላይ ክርክራቸውን ለመመልከት ለነገ መስከረም 8 ቀን 2013 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ