20210302 adwa

ይገረም አለሙ

Irrecha protest, 2nd Oct, 2016

ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የኖረውን የኢሬቻ በዓል ለማክበር ኢትጵያውያን በቢሾፍቱ/አዳማ ከተማ የከተቱት ቅዳሜ መስከረም 21 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ሲሆን፣ በማግስቱ እሁድ ረፋዱ ላይ በምስል ተደግፎ በማኅበራዊ መገናኛ የተሰራጨው ዜና ፈጽሞ ያልተጠበቀ ብቻ ሳይሆን፤ ሊገመት የማይችል ነበር። በአንድ ጣራ ስር ሆነን መርዶውን ከሰማነው መካከል ዕድሜአቸው ስድሳውን የዘለለ አንዲት እናት ለስንቱ እናልቅስ ብለው አንባቸውን አዘነቡት። ሌሎቻችንም በየውስጣችን አለቀስን። ለደቂቃዎች ቤቱ ጸጥ ረጭ አለ። ሁሉም በየራሱ ስሜት ውስጥ ሰምጦ የሚናገር ጠፋ። ዝምታው የተሰበረው ሆራ ኃይቅ ዳር የተሰበሰበ ህዝብ አይደለም ሰላማዊ ተቃውሞ ማሰማት ድንጋይ ቢወረውር ምን ጉዳት እንዳያደርስ ነው በአስለቃሽ ጭስ የሚባረረው በጥይት የሚደበደበው በሚል መልስ የለሽ ጥያቄ ነበር።

ይህም ይረሳ ይሆን!

የቢሾፍቱው እልቂት በአይነቱም በብዛቱም የተለየ ከመሆኑ በቀር ለወያኔ ግድያ፣ ለእኛም ሰምቶ አይቶ እርር ድብን ማለት አዲስ ነገር አይደለም። ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት በእምነት ቦታዎች፣ በት/ት ተቋማት፣ በአደባባይ፣ በእስር ቤቶች፣ ግድያዎች ተፈጽመዋል። ድርጊቱ በተፈጸመ ዕለትና ማግስት ከወያኔ በተቃራኒ ያለን ሁሉ እርር ድብን እያልን እንቃጠላለን፣ በምናገኘው የመገናኛ መንገድ ሁሉ ወያኔን እያወገዝን፤ በቃ ከዚህ በኋላ እያለን እየዛትን፣ እየፎከርን እንዲህ መሆን አለበት፣ ይህ መደረግ አለበት እንላለን። ፖለቲከኞቻችንም በዚህ ቀን እንኳን ድምጻቸው እንዲሰማ፤ ተቃውሞአቸው እንዲበረታ፤ ተጠራርተው በጋራ መጮሁ አልሆን እያላቸው ከየጎጆአቸው ሆነው የወረቀት መግለጫ ያወጣሉ፤ ወይንም ጥቂት ጋዜጠኞችን በቢሮአቸው ጠርተው ውግዘት ተቃውሞአቸውን ያሰማሉ። በተለያየ የዓለም ክፍል፤ በተለይ ደግሞ በሰሜን አሜሪካና በአውሮፓ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም ተጠራርተው ሰልፍ በመውጣት በእልህና በቁጣ ተቃውሞአቸውን ይገልጻሉ። ከዛ ከአንድ ሣምንት በኋላ ሁሉም ይረሳል።

ያለግድያ መኖር የማይችለውና ለችግሮች ሁሉ መፍትሔ፣ ለጥያቄ ሁሉ መልስ ጠመንጃውን አድርጎ የሚያምነው፤ በዚህም ሥልጣኑን ማቆየት የቻለው ወያኔ፤ ውሎ አድሮ ሌላ ግድያ ይፈጽማል፣ ሌላ እልቂት ያደርሳል። ያኔ እኛም ያንን የተለመደ የአንድ ሣምንት ቁጭትና ጩኸት እናሰማና እንረሳዋለን። በእንዲህ ሁኔታ ዙሩ ቀጥሎ የቂሊንጦው ፍጅት በተረሳ ማግስት የቢሸፍቱው እልቂት ተፈጸመ። ያው እንደተለመደው መርዶው ከተሰማበት ቅጽበት ጀምሮ የኢትዮጵያውያን ንዴት፣ እልህ፣ ቁጣ፣ ውግዘት፣ ፉከራ ከያቅጣጫው እየተሰማ ነው፤ ይህም ከአንድ ሣምንት በኋላ ላለመረሳቱ ግን ርግጠኛ መሆን አይቻልም።

ለስንቱ እናልቅስ

ከላይ የገለጽኳቸው እናት በየግዜው የተፈጸሙና ያስለቀሱዋቸውን ድርጊቶች ባለመርሳታቸው ነው ለስንቱ እናልቅስ ያሉት። ፖለቲከኞቻችን ግን አብዛኛዎቹ ትግሉን ሳይሆን ቤተ መንግሥቱን ናፋቂዎቹ የእኝህን እናት ያህል እንኳን ትናንትን ያስታውሳሉ ለማለት አልደፍርም። ያ ቢሆንና ያለፈውን እየረሱ በአዲሱ የሚጩኹ ባይሆኑ ኖሮ ከእንግዲህ በህዝብ ላይ እልቂት ሲፈጸም መቆጣትና መግለጫ ማውጣት ሳይሆን፤ ህዝቡን ከገዳዮች መገላገል ነው ብለው ተጠራርተው መክረውና ዕቅድ አውጥተው መታገል በቻሉ ነበር።

ወያኔ እልቂት የሚፈጽመው ጾታ ዕድሜ ብሔር ሳይመርጥ ለሥልጣኔ ያሰጋኛል ባለው ላይ ሁሉ ነው። ከየትኛውም ብሔር ይሁን፣ የትኛውንም ኃይማኖት ይከተል፤ ህዝብ ያስተባብራል፣ ለወንበራችን ያሰጋል ተብሎ የተገመተ ማናቸውም ሰው እስር ወይንም ግድያ ይደገስለታል። እንዲህ ኢትዮጵያውያንን ሁሉ እየገደለ የመጣና አሁንም እየገደለ ያለ ወደ ፊትም የሚቀጥል የጋራ ጠላትን መከላከልም ሆነ ማስወገድ የሚቻለው ድር ቢያብር አንበሳ ያስር ብሎ በአንድነት በመሰለፍ ቢሆንም፤ ለዚህ መብቃት አልተቻለም።

መተባበር ባለመቻሉ፤ ወያኔዎች እየገደሉ ይኖራሉ

ጋን በጠጠር ይደገፋል እንዲሉ ሁሉም ያለውን ትንሽም ይሁን ትልቅ አቅም አስተባብሮ በየግል አቋሙ ተከባብሮና የጋራ አጀንዳ ቀርጾ ለመታገል ፈቃደኛ ባለመሆኑ፤ በሁሉም ዘርፍ ደካማና አነስተኛ የሆነው የተቃውሞ ጎራ ወያኔን የሚገዳደር አቅም ሊፈጥር አልቻለም። የዚህ አብዩ ምክንያት ተደጋግሞ እንደተነገረውና እንደተጻፈው፤ ትናንሽ ዘውግ በኪሱ ይዞ የሚዞረው መብዛቱ ነው። በሥልጣን ጥም የናወዙ ፖለቲከኞች በህዝብ ላይ የሚፈጸመውን እልቂት እያዩ እንኳን ከዚህ በሽታቸው ለመገላገል ሲሞክሩ አይታዩም።

አደረጃጀትን፣ የትግል ስልትን፣ … ወዘተ ምክንያት በማድረግ መለያየቱ በትንሹም ቢሆን ምክንያት ሊሰጠው ይችላል። በተመሳሳይ የትግል ስልት በአንድ ብሔር ስም አራት አምስት ድርጅት መመስረቱ ግን ለምን የሚያሰኝ ነው። በአንድ ብሔር ስም ተለያይቶ ድርጅት ከመሰረቱ በኋላ ደግሞ የሚታየው የመጀመሪያው ጥፋት፣ ርስ በርሳቸው አለመተባበራቸው፤ ይህም ቢቀር አለመከባበራቸው ነው። አንተም በመንገድህ እኔም በመንገዴ ከመባባል ይልቅ፤ አንዱ የአንዱ አደናቃፊ መሆናቸው ደግሞ ሁለተኛው ጥፋት ሲሆን፤ ሦስተኛው ጥፋት በኢትዮጵያዊነት ተደራጅተው በሚታገሉት ላይ ላይ ቃታ ለመሳብም ሆነ ድንጋይ ለመወርወር አቅሙ ባይኖራቸውም የሚያካሂዱት የፖሮፓጋንዳ ዘመቻ ነው። በዚህ መልኩ ወያኔን እንታገላለን እያሉ ለወያኔ ዕድሜ መራዘም መሥራት።

መተባበር ያለመቻል ዋናው ችግር የሥልጣን ጉዳይ መሆኑ ከታወቀ ውሎ አድሯል። ግን ሁሉም ሊቀመንበር ወይም ፕሬዝዳንት የሚባልበትን ድርጅትና ሥልጣኑን እንደያዘ፤ ህዝብን ከእልቂት ለመታደግና በዘላቂነት ከወያኔ አገዛዝ ለመገላገል፤ ብሎም በድል ማግስት ሊመሰረት ስለሚገባው ሥርዓት ምንነትን እንዴትነት ተነጋግሮ የጋራ መርሃ ግብር ዘርግቶ ከድል እስከ ሽግግር የሚያደርስ የዘመቻ ዕቅድ አውጥቶ መታገል ምን ይገዳል። የቢሾፍቱው እልቂት እንደተሰማ፤ ሌሎቹ ቢቀሩ የኦሮሞ ስም የያዙት ድርጅቶች ወዲያውኑ ተጠራርተው ሸንጎ ይቀመጣሉ፣ ከዚህ የባሰ ምን እስኪመጣ ነው የምንጠብቀው ተባብለው የየግል ጉዳያቸውን ጥለው አንድ ሆነው ለመውጣት ይመክራሉ ብየ ጠብቄ ነበር። ግና ምን ያደርጋል ፖለቲከኞቹ በህዝብ ላይ የሚፈጸመው እልቂት ለስንቱ እናልቅስ ያሉትን እናት ያህል እንኳን የሚሰማቸው አልሆኑምና፤ ዛሬም እዛው የትናንት ቦታቸው ላይ እንደቆሙ ናቸው።

የቢሸፍቱውን እልቂት ማውገዝ ከስሜት በላይ መሆን አለበት

እልቂቱን ተከትሎ የሚሰማው ተቃውሞ ውግዘትና ፉከራ ስሜት ብቻ ከሆነ እንደስከዛሬው ሁሉ ከሣምንት በኋላ ይረሳል። የለም ከዚህ በላይ ምን እስኪሆን እንጠብቃለን ከተባለ የሚነገረው የሚጻፈው ሁሉ የሚረሳ ሳይሆን፤ ወደ እምነት የሚሸጋገር ይሆንና የሚከተሉት ተግባራዊ ይሆናሉ።

የፖለቲካ ድርጅቶች፣

ኢትዮጵያ የብዙ ብሔረሰቦች ሀገር እንደመሆኗ በኢትዮጵያዊነት መተባበር እንደማይቻል ከልማዳችን አይተነዋል። በዚህ ዙሪያ ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ፈልጎ መፍትሔ አፈላልጎ ለመነሳት ደግሞ ግዜ የለም። አማራ ግን አንድ ነው፣ ኦሮሞም አንድ ነው፣ ሌሎችም እንደዚሁ። በመሆኑም የትግል ስትራቴጂ ልዩነት እስከሌለ ድረስ በአንድ ብሔር/ብሔረሰብ ስም አራት አምስት ደርጅት መመስረት የግለሰቦች የግል ፍላጎት ከመሆን የዘለለ ምክንያት ሊቀርብለት አይችልም። የግለሰቦችን የሥልጣን ፍላጎት ለማርካት ተብሎ ህዝብን እየፈጀ ያለውን ሥርዓት ለማስወገድ የሚደረገውን ትግል ማዳከም ደግሞ በምንም መመዘኛ ተቀባይነት የለውምና፤ ለአንድ አማራ አንድ ፓርቲ፣ ለአንድ ኦሮሞ አንድ ፓርቲ፣ … ወዘተ እንዲሆን ለማድረግ ግዜ ሳይሰጡ መሥራት።

ከዚህ በተጨማሪ በርግጥ ለነጻነት የሚታገሉ ድርጅቶች በወያኔ መወገድና የትግሉ ውጤት ኢትዮጵያን ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚያበቃ በመሆኑ ላይ ተስማምተው፤ አንዱ የሌላው እንቅፋት ሳይሆን እየተናበቡ በየሚያምኑበት መንገድ ትግሉን መቀጠል።

የየፓርቲዎቹ አባላትና ደጋፊዎች፤

አባልነታችሁም ሆነ ደጋፊነታችሁ በስሜት ሳይሆን በእምነትና በእውነት ላይ የተመሰረተ ይሁን። እናም ድርጅታሁ ለነጻነት ትግሉ ምን አዎንታዊ፣ ምን አሉታዊ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሆነ ፈትሹ። በአንድ ብሔረሰብ ስም አራት አምስት ድርጅት ስለተመሰረተበት ምክንያትም መርምሩ። ከዛም የዓላማና የትግል ስትራቴጂ ልዩነት የሌላቸው አንድ እንዲሆኑ፣ አንድ መሆን የማይችሉት ደግሞ አንዱ ለሌላው እንቅፋት ሳይሆን ተደጋግፈውና ተከባብረው እንዲሠሩ አስገድዱ።

ዲያስፖራው፤

እስከ ዛሬ ስር ሰዶ የነበረው ሆድና ጀርባ የመሆንና የጎሪጥ መተያየት ሀገር ቤት ህዝቡ ባሳየው አንድነት ረገብ ያለ ቢሆንም፤ ገና ይቀረዋል። እናም ጨርሶ ለማስወገድ ታሪክ እየመዘዙ መነታረኩ፣ ሰልፍ ላይ የሚያዙ ሰንደቅ ዓላማዎችና የሚስተጋቡ መፈክሮች ምክንያት እየሆኑ መዋረፉ ተለያይቶ ሰልፍ መውጣትም ሆነ ማዶና ማዶ ሆኖ የማይደምቅ ጩኸት ማሰማት ከእንግዲህ መኖር የለበትም። የህዝብ ልጆች ቢሾፍቱ ላይ በደማቸው ያቀለሙት አንድነት፤ ከእንግዲህ በምንም በማንም አይቀለበስም። ስለሆነም የዲያስፖራው የከእንግዲህ ተግባር አንድ የሚያደርጉንን ጉዳዮች ውኃ እያጠጣን ማሳደግ እንጂ፤ የሚያለያዩንን በመፈለግ መድክም መሆን የለበትም።

ወያኔ በሥልጣን ላይ እስካለ ግድያ አይቀርም። እኛም በመጣንበት የሃያ አምስት ዓመት መንገድ መጓዛችንን ከቀጠልን ግድያን ማስቆምም ሆነ ከወያኔ መገላገል አይቻለንም። ስለሆነም መንገዳችንም ሆነ አካሄዳችን፣ ሥራችንም ሆነ አስተሳሰባችን መለወጥ አለበት። ለለውጥ ለመብቃት ደግሞ ከተቻለ አንድ መሆን፣ ካልተቻለም መደጋገፍና መተባበር፣ ይህም ካልተቻለ በአንድ ጎራ ተሰልፎ ርስ በርስ ከመጠቃቃትና አንዱ ለሌላው እንቅፋት ከመሆን መታቀብ ያስፈልጋል። ወያኔን ያወገዘ ሁሉ ተቀዋሚ ድርጅት የፈጠረ ሁሉ የነጻነት ታጋይ አይደለምና፤ የነጻነት ትግሉ እንዳይጎዳ እውነተኛ ታጋዮች ለአጉል መስዋዕትነት እንዳይዳረጉ ስንዴውን ከእንክርዳድ ለይቶ ማወቅና መጠንቀቅም አስፈላጊ ነው።

ተቀዋሚው ማድረግ ያለበትን ባለማድረግ ከዚህ በኋላ ወያኔ ጉልበት ኖሮትም ይሁን በአልሞት ባይ ተጋዳይነት በህዝብ ላይ እልቂት ቢፈጽም ከወያኔ ባልተናነሰ ተጠያቂ ይሆናል።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!