Prof. Mesfin WoldeMariam's funeral

የፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ሥርዓተ ቀብር በመንበረ ጽባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጸመ

ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትና ታዋቂ ሰዎች ተገኝተዋል

ኢዛ (ማክሰኞ መስከረም ፳፮ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. October 6, 2020)፦ የእውቁ ምሁርና የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ የፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ሥርዓተ ቀብር ዛሬ ማክሰኞ መስከረም 26 ቀን 2013 ዓ.ም. በክብር ተፈጽሟል። ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትና ታዋቂ ሰዎች ተገኝተዋል።

ከቀብር ሥርዓቱ ቀደም ብሎ ለዓመታት ባስተማሩበት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ልደት አዳራሽ፤ ስለአገር እና ስለሰብአዊ መብት እንዲሁም በሕይወት ዘመናቸው ያበረከቱትን አስተዋጽኦ ተዘክሯል።

በልደት አዳራሽ የሽኝት ፕሮግራም የእርሳቸውን ሰብዕና ያመለከቱ ንግግሮች በታዋቂ ሰዎች የቀረቡ ሲሆን፤ በተለይም ፕሮፌሰር መስፍን በኢትዮጵያ እና በኢትዮጵያዊነት የነበራቸው ጽኑ አቋም ለዜጎች ተቆርቋሪነታቸውና ለሰው ልጆች የሰብአዊ መብት ጥበቃ ያደረጉዋቸውን የዓመታት አበርክቶ በተለያዩ ምሳሌዎች የተጠቀሰበት መድረክ ነበር።

ያመኑበትን በመናገር ለአገር ይበጃል ያሉትን ሐሳብ ያለምንም ፍራቻ በመግለጽ የሚታወቁት ፕሮፌሰር መስፍን፤ ለትውልድ የሚተርፍ አርኣያነታቸው ጎልቶ እንዲታይ ያደረገው የልደት አዳራሹ የሽኝት ፕሮግራም ከተጠናቀቀ በኋላ፤ በመንበረ ጽባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሥርዓተ ቀብራቸው ተፈጽሟል።

የሰብአዊ መብት ተሟጋቹን ፕሮፌሰር መስፍንን ለመሸኘት በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች የተገኙ ሲሆን፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔን ጨምሮ፤ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዝዳንትና ሌሎች ባለሥልጣናት የተገኙበት ነበር።

የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ፣ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢና ሌሎችም ታዋቂ ሰዎች ተገኝተው ነበር። በዕለቱ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ በወኪላቸው የአበባ ጉንጉን ተቀምጧል።

በፕሮፌሰር መስፍን ሕልፈተ ሕይወት ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይኾን ዓለም አቀፍ ተቋማት ጭምር ኀዘናቸውን ገልጸዋል። ከእነዚህ ውስጥም አምነስቲ ኢንተርናሽናል ይገኝበታል።

በዚህ የቀብር ሥርዓት ላይ እንደቅሬታ እየቀረበ ያለው፤ በኦርቶዶክስ እምነት ተከታይነታቸው እና ይህንንም በማቀንቀን በሚታወቁት የፕሮፌሰር መስፍን ሥርዓተ ቀብር ላይ የቤተክርስቲያኗ ጳጳሳት አለመገኘታቸው ነው።

እውቁ ምሁርና የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም በ91 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ባለፈው ሳምንት ረቡዕ መስከረም 20 ቀን 2013 ዓ.ም. እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ