የህዳሴው ግድብ ጽ/ቤት ዋና ዳይሬክተር ተነስተው ዶ/ር አረጋዊ በርሄ ተተኩ
ዶ/ር አረጋዊ በርሄ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር
የቀድሞዋ ዳይሬክተር ሕወሓት ጥሪ ካደረገላቸው አባላቱ አንዷ ነበሩ
ኢዛ (ሐሙስ ጥቅምት ፭ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. October 15, 2020)፦ ከሕወሓት ቀደምት ታጋዮችና በኋላም ከሕወሓት አካሔድ በተቃራኒ በመቆም፤ የራሳቸውን ፓርቲ መሥርተው በመታገል የሚታወቁት የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) ሊቀመንበር ዶ/ር አረጋዊ በርሄ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ኾነው ተሾሙ።
ዶክተር አረጋዊ በርሄ በአገሪቱ የሚገኘውን ትልቁን ሜጋ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት በዋና ዳይሬክተርነት እንዲመሩ የተሾሙት በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ነው።
ዶ/ር አረጋዊ አሁን በዳይሬክተርነት የተሾመውበት የሥራ ኃላፊነት ላይ ቀደም ሲል ሲሠሩ የነበሩት የሕወሓት አባል የነበሩት ወይዘሮ ሮማን ገብረሥላሴ ነበሩ።
ወ/ሮ ሮማን በቅርቡ ሕወሓት በፌዴራል መንግሥት በኃላፊነት የሚሠሩና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የኾኑ አባሎቹን ኃላፊነታቸው ለቀው ለፓርቲው ሪፖርት እንዲያደርጉ በስም ከተጠቀሱት መካከል አንዷ ናቸው።
ዶ/ር አረጋዊ በርሄ ከ29 ዓመታት በፊት (እ.ኤ.አ. 1991) ከሕወሓት በመነጠል በስደት የቆዩና በኋላም ትዴፓን በመመሥረት በውጭ ሲታገሉ የቆዩ ሲሆን፤ ከሁለት ዓመታት ተኩል በፊት በተደረገው ለውጥ ወደ አገር በመምጣት በሰላማዊ መንገድ እየተንቀሳቀሱ የቆዩ ናቸው።
ዶ/ር አረጋዊ ይህንን ትልቅ የአገር ፕሮጀክት የኾነውን ጽ/ቤት እንዲመሩ መሾማቸው ከለውጡ ወዲህ እንዲህ ባለው ሁኔታ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚሾሙ የተፎካካሪ ፓርቲዎች አመራሮችን ቁጥር ከፍ እያደረገው መምጣቱን አመላክቷል።
ከዚህ ቀደም ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና የኢቢሲ ቦርድ አባል እንዲኾኑ መሰየማቸው ቀድሞ የሚጠቀስ ሲሆን፤ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቦርድ አባል ኾነው በመሾም እየሠሩ ነው። በቅርቡም የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በመኾን የተሾሙት ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስም በተመሳሳይ በጠቅላይ ሚኒስትሩ መሾማቸው ይታወሳል። (ኢዛ)



