በተለየ አሳሳል ጥበባቸው የሚታወቁት ሰዓሊ ለማ ጉያ አረፉ

ሰዓሊ ለማ ጉያ
በኢትዮጵያ ሥነ ሥዕል ታሪክ የተለየ አሻራ አሳርፈዋል
ኢዛ (ሰኞ ጥቅምት ፲፮ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. October 26, 2020)፦ በኢትዮጵያ ሥነ ሥዕል ታሪክ የተለየ አሻራ በማሳረፍ ጭምር የሚታወቁት ሰዓሊ ለማ ጉያ በ92 ዓመታቸው አረፉ።
ለየት ባለ የአሳሳል ጥበባቸው፤ በተለይም በፍየል ቆዳ ላይ በመሳል የሚታወቁት ሰዓሊ ለማ ጉያ፤ በኢትዮጵያ በሥነ ሥዕል ታሪክ ውስጥ ሲያበረክቱት ለቆዩት አስተዋጽኦ ከመንግሥትና ከተለያዩ ተቋማት እውቅናና ክብር የተቀበሉ ናቸው።
ሰዓሊው በይበልጥ በሚታወቁበትና ላለፉት 65 ዓመታት በፍየል ቆዳ ላይ የሳሉዋቸው ሥዕሎች ከ10 ሺህ በላይ እንደሚኾን አንዳንድ መረጃዎች ያመለክታሉ።
በፍየል ቆዳ ላይ የሚስሏቸው ሥዕሎች በዋናነት የኢትዮጵያና የአፍሪካ መሪዎችንና ታዋቂ ሰዎችን ምስል ጨምሮ፤ የብሔር ብሔረሰብ አኗኗር፣ ወግና ባህል፤ እንዲሁም የኢትዮጵያን የተፈጥሮ ሀብቶችን አብዝተው በመሳል ይታወቃሉ።
ይህ የሥነ ሥዕል ችሎታቸውና ትሩፋታቸው፤ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይኾን በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅናና ክብር የተሰጠው ነው።
ለዘመን ተሻጋሪ ሥራቸውና በሥነ ሥዕል ላበረከቱት አስተዋጽኦ የተለያዩ የክብር እውቅና ያገኙት ሰዓሊ ለማ ጉያ፤ ከጅማ ዩኒቨርሲቲ የሰጣቸው የክብር ዶክትሬት ተጠቃሽ ነው።
በቢሾፍቱ (ደብረዘይት) ከተማም ለማ ጉያ በመባል የሚታወቅ የሥነ ጥበብ ማዕከል በመገንባት ሥዕሎቻቸውን ለሕዝብ በማሳየትም ይታወቃሉ። የኢትዮጵያ ዛሬ ድረገጽ ዝግጅት ክፍል ለመላው ቤተሰቦቻቸው፤ ዘመዶቻቸው፤ ለወዳጆችና አድናቂዎቻቸው መጽናናትን ይመኛል። (ኢዛ)