Ambassador Ahadu Sabure

አምባሳደር አሐዱ ሳቡሬ

“አሐዱ ሳቡሬ፣ አጠገበኝ ወሬ” በመባል ይጠሩ ነበር

ኢዛ (ሰኞ ኅዳር ፰ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. November 18, 2019)፦ አንጋፋው ጋዜጠኛና ዲፕሎማት አምባሳደር አሐዱ ሳቡሬ በአሜሪካን አገር በሎስ አንጀለስ ከተማ በተወለዱ በዘጠና አራት ዓመታቸው ሐሙስ ኅዳር 4 ሌሊት ለዓርብ አጥቢያ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።

ጋዜጠኛ አሐዱ ገና በአስራ ሦስት ዓመታቸው የጣሊያንኛና ሱማልኛ ቋንቋዎችን በማስተርጎም ደምወዝ እየተከፈላቸው ሥራ የጀመሩ ሲሆን፣ ከጣሊያን ወረራ በኋላም የድሬዳዋ ማዘጋጃ ቤት ሲከፈት በጽሕፈት ሥራ ተቀጥረው ሠርተዋል።

ቀጥሎም ወደ አዲስ አበባ በመሔድ በማስታወቂያ ሚኒስቴር በጋዜጠኝነትና በሬድዮ ዜና አንባቢነት ተቀጥረው ለረጅም ዓመታት የሠሩ ሲሆን፣ በኋላም በሱማሊያና በጅቡቲ በአምባሳደርነት አገልግለዋል። በ1966 ዓ.ም ጠ/ ሚኒስትር እንዳልካቸው መኮንን የጠ/ሚኒስትርነት ሥልጣን ሲይዙ፣ የካቢኔ አባል ኾነው በማስታወቂያ ሚኒስቴር በሚኒስትርነት አገልግለዋል።

1947 ዓ.ም. “የዓለም መስተዋት” በሚል ለሕዝብ መጽሐፍ ያበረከቱት አሐዱ ሳቡሬ የተወለዱት በሐረር ክፍለ አገር አቢጋራ በሚባል ቦታ በ1917 ዓ.ም. ሲሆን፣ የዘጠና አራት አመት የዕድሜ ባለጸጋ ነበሩ። “የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግሥት ፍጻሜና የደርግ አነሳስ” የሚል መጽሐፍም ለንባብ አብቅተዋል። ከዕድሜቸው ውስጥ አንድ ሦስተኛውን የኖሩት በአሜሪካ አገር ነበር። የፊታችን ዓርብ ሥርዓተ ቀብራቸው በሎስ አንጀለስ እንደሚፈጸም ለማወቅ ችለናል።

“አሐዱ ሳቡሬ፣ አጠገበኝ ወሬ” የሚለውን መጠሪያቸውን ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ ያወጡላቸው በመሆኑ የነጋድራስ ተሰማ ስም ከአሐዱ ሳቡሬ ጋር ተያይዞ ይጠራል። ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ የኢትዮጵያ የስፖርት ፌዴሬሽን ኮሚሽነርና የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሪሽን ፕሬዝዳንት የነበሩት የአቶ ይድነቃቸው ተሰማ አባት ነበሩ። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ