አንድነት በዓመታዊ በጀቱ ከኢትዮጵያ ፓርቲዎች የመሪነቱን ሥፍራ ያዘ
Ethiopia Zare (እሁድ ጥቅምት ፪-2 ቀን ፳፻፩-2001 ዓ.ም. October 12, 2008)፦ አንድነት ፓርቲ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዓመታዊ የበጀት ታሪክ ውስጥ በአንደኝነት ደረጃ ላይ ሊያስቀምጠው የሚችለውን የ7 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ዓመታዊ በጀት ለያዝነው 2001 ዓ.ም. መያዙ ታወቀ።
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ዓርብ መስከረም 30 ቀን 2001 ዓ.ም. ጠዋት በተለምዶ ”መስከረም ማዞሪያ” ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኘው ጽሕፈት ቤቱ በጠራው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ፤ ፓርቲው በያዝነው 2001 ዓ.ም. ዓመታዊ በጀቱ 7 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር እንደሆነና የሚቀጥለው ዓመት በሚደረገው ምርጫ ለመሳተፍ ጠንካራ ዝግጅቶችን እንደሚያደርግ አሳውቋል።
በኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች ታሪክ ውስጥ እስካሁን ድረስ ዓመታዊ በጀቱ 7.3 ሚሊዮን ብር የደረሰ ፓርቲ እንደሌለ ታውቋል። በዚሀም ምክንያት አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ በዓመታዊ በጀቱ የመሪነቱን ሥፍራን እንደያዘ ለመገንዘብ ችለናል።
ይህንን 7.3 ሚሊዮን ብር ዓመታዊ በጀቱን ለማሟላት ያቀደው ከፓርቲው አባላት መደበኛ መዋጮ፣ ከሀገር ውስጥና ከውጭ ሀገር ከሚገኙ ደጋፊዎች የድጋፍ ገንዘብ በማሰባሰብ፣ እንዲሁም የተለያዩ ቁሳቁሶችን በመሸጥ መሆኑን አስታውቋል።
በዚሁ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ በመላው ሀገሪቱ እስከ ወረዳ በዘለቀ ሁኔታ 117 ቅርንጫፍ መስሪያ ቤቶችን በሚቀጥሉት ሦስት ወራት ፓርቲው እንደሚከፍት አስታውቋል። በማዕከላዊና በክልሎች የሚያደርገውን እንቅስቃሴ በይፋ የሚጀምረው ጥቅምት 8 ቀን 2001 ዓ.ም. መሆኑም ታውቋል።
በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ በ2002 ዓ.ም. ሀገር አቀፍ ምርጫ ፓርቲው እንደሚሳተፍ የፓርቲው አመራሮች አስታውቀዋል። በምርጫው የሚሳተፈውም የምርጫ ጊዜ የፖለቲካ ፓርቲ ለመሆን ብሎ ሳይሆን፤ አሸናፊ ሊያደርጉት የሚችሉትን ዝግጅቶች አጠናቅቆ መሆኑን በጋዜጣዊ መግለጫው ወቅት ለተገኙት ለጋዜጠኞች ገልጧል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ዛሬ እሁድ ጥቅምት 2 ቀን 2001 ዓ.ም. የአንድነት ፓርቲ አመራሮች ለመጀመሪያ ጊዜ በውጭ ሀገር ለሚገኙ የኢትዮጵያውያ የመገናኛ ብዙኀን ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚሰጡ የአንድነት የሰሜን አሜሪካ የድጋፍ ሰጪ ማኅበር ለኢትዮጵያ ዛሬ በላከው የጥሪ መልዕክት አስታውቋል። ጋዜጣዊ መግለጫው የሚካሄደው በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 2 ሰዓት ከ45 ደቂቃ (1:45pm EST ወይንም 19፡45 ሴንትራል ዩሮፒያን ታይም) ጀምሮ በሚካሄድ የቴሌኮንፈረንስ መሆኑን ለማወቅ ችለናል።



