Jawar Mohammed (L), Bekele Gerba (R)

አቶ ጃዋር መሐመድ (በግራ)፣ አቶ በቀለ ገርባ (በቀኝ)

“አሁን ባለው ሁኔታ በእነርሱ ላይ ጥቃት ቢፈጸም አገሪቷ የባሰ ችግር ውስጥ ትግባለች በማለት ነው ፍርድ ቤት ያልቀረቡት” አቶ ሃምዛ

ኢዛ (ማክሰኞ ጥቅምት ፳፫ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. November 3, 2020)፦ አቶ ጃዋር መሐመድ እና አቶ በቀለ ገርባ ዛሬ ማክሰኞ ጥቅምት 23 ቀን 2013 ዓ.ም. ፍርድ ቤት በነበራቸው ቀጠሮ ላይ ለደኅንነታችን እንሰጋለን በማለት ችሎት ሳይቀርቡ መቅረታቸው ተገለጸ።

በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ ችሎት ቀጠሮ የነበራቸው እነአቶ ጃዋር መሐመድ ለዛሬ ተቀጥረው የነበረው፤ የባንክ አካውንት እና የንብረት እግድን በተመለከተ የመልስ መልስ ለመስጠት ነበር።

ኾኖም እነአቶ ጃዋር ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ በመቅረታቸው ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል። እነአቶ ጃዋር መሐመድ በዕለቱ ፍርድ ቤት ያልቀረቡበትን ምክንያት ፍርድ ቤቱ ጥያቄ ያቀረበ ሲሆን፤ በዚህ መዝገብ ተጠርጥረው ከተከሰሱት መካከል አንዱ የኾኑት አቶ ሃምዛ አድናን፤ እነአቶ ጃዋር መሐመድና አቶ በቀለ ገርባ ፍርድ ቤት ያልቀረቡት ለደኅንነታቸው ሰግተው ነው ብለዋል።

አሁን ካለው የአገሪቱ ጸጥታ ሁኔታ አንጻር ትልቅ ሥጋት ያላቸው በመኾኑ በቀጠሮ አንቀርብም ማለታቸውን አቶ ሃምዛ ለፍርድ ቤቱ ገልጸዋል። አሁን ባለው ሁኔታ በእነርሱ ላይ ጥቃት ቢፈጸም አገሪቷ የባሰ ችግር ውስጥ ትግባለች በማለት ጭምር ከቀጠሮው ስለመቅረታቸው ለፍርድ ቤቱ አክለው አስረድተዋል።

ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን ለማየት ለኅዳር 15 ቀን 2013 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ