ጽንፈኛው ሕወሓት ወደ አስመራ ሮኬቶች መተኮሱ ተሰማ
አስመራ
“ዛሬ ሕወሓት በኦፊሴል ኤርትራን ለጦርነት ጋብዟል፤ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ክብር ስንል እንታገሳለን” የኤርትራ ፕሬስ
ኢዛ (ቅዳሜ ኅዳር ፭ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. November 14, 2020)፦ የሕወሓት ጽንፈኛ ቡድን ወደ አስመራ ሮኬቶች መተኮሳቸው ታውቋል።
ሮኬቶቹ በአስመራ የት እንዳረፉና ያደረሱትን ጉዳት የተመለከተ የተሰጠ መረጃ ባይኖርም፤ እንደ አልጀዚራ ያሉ የመገናኛ ብዙኀን ወደ አስመራ ሮኬት ስለመወንጨፉ አረጋግጠናል ብለዋል።
“የኤርትራ ፕሬስ” በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት እንዳሰፈረው ከኾነ፤ ሕወሓት አስመራን በሮኬቶች ያጠቃች መኾኑን ዘግቧል። ድርጊቱ ኤርትራን ወደ ጦርነት የማስገባት ዓላማ ያለው መኾኑን አስረድቷል። “ዛሬ ሕወሓት በኦፊሴል ኤርትራን ለጦርነት ጋብዟል፤ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ክብር ስንል እንታገሳለን” ብሏል የኤርትራ ፕሬስ።
ጁንታው የሕወሓት ቡድን አስመራ ውስጥ የሚገኙ የመኖሪያ መንደሮችን በመደብደብ ከኤርትራ አጸፋዊ ምላሽ እንዲሰጠውና በዚህም ሳቢያ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጣልቃ እንዲገባ የነደፈው ስትራቴጂ እንደኾነ የኤርትራ ፕሬስ ዘግቧል። ስሌቱ የተሳሳተ መኾኑን ጠቅሶ፤ ኤርትራ ራስዋን ከአሸባሪዎች የመከላከል ሙሉ መብት ያላት መኾኑን ጠቅሷል።
ኤርትራ ምዕራባውያን አሸባሪውን የሕወሓት ቡድን ማውገዝ እንዳለባቸው ዘገባው አክሎ ጠቅሷል። (ኢዛ)



