20210302 adwa

National Bank of Ethiopia

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ

በክልሉ የሚገኙ ከ600 በላይ የባንክ ቅርንጫፎች የሚከፈቱበት ሁኔታ እየታየ ነው

ኢዛ (ረቡዕ ኅዳር ፳፫ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. December 2, 2020)፦ በትግራይ ክልል ውስጥ በሚገኙ የባንክ ቅርንጫፎች አካውንት ከፍተው፤ ከትግራይ ክልል ውጭ አካውንታቸውን ማንቀሳቀስ እንዳይችሉ ተጥሎ የነበረው እገዳ ተነስቶ፤ በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል አካውንታቸውን እንዲያንቀሳቅሱ ተፈቀደ።

በትግራይ ክልል ውስጥ ሲካሔድ የነበረውን የሕግ ማስከበር ሥራ ተከትሎ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከጸጥታ ሁኔታ ሥጋት ጋር ተያይዞ ለባንኮች አሠራር አመቺ ባለመኾኑ፤ በትግራይ ክልል ባሉ የባንክ ቅርንጫፎች አካውንት የከፈቱ ደንበኞች በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ገንዘብ እንዳይንቀሳቀሱ አድርጎ ነበር።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ዛሬ ረቡዕ ኅዳር 23 ቀን እንዳስታወቀው፤ በፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በወንጀል ተጠርጥረው ሒሳባቸው እንዳይንቀሳቀስ ከተደረጉት ውጭ፤ በትግራይ ክልል በሚገኙ ባንኮች አካውንት የከፈቱና ከትግራይ ውጭ ያሉ ደንበኞች በያሉበት አካባቢ ባሉት ባንኮች አካውንታቸውን እንዲያንቀሳቅሱ ተፈቅዷል። ይህም ከዛሬ ኅዳር 23 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ እንደሚተገበርም አስታውቋል።

ከ600 በላይ የባንክ ቅርንጫፎች የሚገኙበት የትግራይ ክልል የሕግ ማስከበር ከተጀመረበት ጊዜ ወዲህ አገልግሎት ማቋረጣቸው የሚወስ ሲሆን፤ እነዚህ ቅርንጫፎች ከማዕከል ያላቸው ግንኙነትም ተቋርጦ ቆይቷል።

እነዚህን ቅርንጫፎች ሥራ ለማስጀመር ባንኩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተነጋገረ መኾኑንም ገልጿል።

የጸጥታ ሁኔታ ለባንኮች አመቺ በኾነባቸው የክልሉ ከተሞች የባንክ አገልግሎቱን መልሶ ለመጀመር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሠራ መኾኑን የገለጸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፤ የጸጥታ ሁኔታ አመቺ ባልኾነባቸው ቦታዎች የባንክ ቅርንጫፎች ተዘግተው የሚቆዩ መኾኑንም አመልክቷል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!