የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ 27 ሚሊዮን ዶላር ተጭበረበረ
Ethiopia Zare (እሁድ ጥቅምት 16 ቀን 2001 ዓ.ም. October 26, 2008)፦ በዚህ ሣምንት ኒውዮርክ (አሜሪካ) ከሚገኘው ሲቲ ባንክ ውስጥ ገንዘብነቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሆነ 27 ሚሊዮን ዶላር ተጭበረበረ። ገንዘቡን ሲያጭበረብሩ የተያዙት ናይጄሪያውያን በቁጥጥር ስር ውለዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በራሱ አካውንት ቁጥር በሲቲ ባንክ ተቀማጭ ገንዘብ ያለው ሲሆን፣ ይህንን ገንዘብ ሦስት ናይጄሪያውያን እንዳጭበረበሩት ባለፈው ሣምንት ኀሙስ ተገልጿል።
ባንኩ እንደገለፀው ከሲቲ ባንክ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን አጭበርባሪዎቹ እንዲታወቁ ያደረገ ሲሆን፣ የገንዘቡ መጭበርበርም በኢትዮጵያ ሀብት ላይ ምንም ለውጥ እንደማያመጣ ገልጸዋል።
ምክንያቱም ችግሩ የተፈጠረው በኢትዮጵያ በኩል ባለመሆኑና በዚሁ ጉዳይ ላይም ከሲቲ ባንክ ጋር በመነጋገር ከስምምነት ላይ በመድረሱ ነው።
እስከ ኀሙስ ጥቅምት 13 ቀን 2001 ዓ.ም. ድረስ 10 ሚሊዮን ዶላር ወደ ብሔራዊ ባንክ አካውንት ውስጥ መግባቱን ገልጿል።
በኢትዮጵያ የሚገኙ ብሔራዊ ባንክን ጨምሮ የመንግሥት እና የግል ባንኮች ከውጭ ባንኮች ጋር አብሮ ከመሥራታቸውም በተጨማሪ አካውንት አላቸው።