ፖለቲከኛ እና ደራሲ አንዳርጋቸው ጽጌ የመቶ ሺህ ብር ቼክ ለመከላከያ ውጭ ግንኙነት ዋና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ብርጋዲየር ጄኔራል ቡልቲ ሲያስረክቡ

ፖለቲከኛ እና ደራሲ አንዳርጋቸው ጽጌ የመቶ ሺህ ብር ቼክ ለመከላከያ ውጭ ግንኙነት ዋና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ብርጋዲየር ጄኔራል ቡልቲ ሲያስረክቡ (ፎቶ፤ መከላከያ ሚኒስቴር)

ሕወሓት በአገር መከላከያ ሠራዊቱ ላይ በተኛበት የፈጸመውን እጅግ አስከፊና አሳዛኝ ጥቃት አውግዘዋል

ኢዛ (ሐሙስ ኅዳር ፳፬ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. December 3, 2020)፦ ራሳቸውን ከፖለቲካ ፓርቲ አባልነት ያገለሉት ፖለቲከኛ እና ደራሲ አንዳርጋቸው ጽጌ፤ ከአዲሱ መጽሐፋቸው ሽያጭ ገቢ ካገኙት ላይ የአንድ መቶ ሺህ ብር ቼክ ለመከላከያ ሚኒስቴር አበረከቱ።

ባለፈው ሳምንት የተመረቀው የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ “የታፋኙ ማስታዎሻ” የተሰኘውና ባለ 308 ገጽ መጽሐፍ ሲሆን፤ ዛሬ ሐሙስ ኅዳር 24 ቀን 2013 ዓ.ም. የአንድ መቶ ሺውን ቼክ ደራሲው ያስረከቡት ለመከላከያ ውጭ ግንኙነት ዋና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ብርጋዲየር ጄኔራል ቡልቲ ታደሰ ነው።

በርክክቡ ላይ ፖለቲከኛ እና ደራሲ አንዳርጋቸው፤ ሕወሓት በአገር መከላከያ ሠራዊቱ ላይ በተኛበት የፈጸመውን እጅግ አስከፊና አሳዛኝ ጥቃት አውግዘዋል። ሠራዊቱ በገዛ ወገኖቹ በተፈጸመበት ጥቃት ለሞቱትና ለአካል ጉዳት የተዳረጉት የመከላከያ ቤተሰቦች ላይ ከፍተኛ ችግርና መከራ መተዉ እንደማይቀር በመግለጽ፤ ሠራዊቱንና ቤተሰቦቻቸውን ከጎናችሁ ነን ለማለት የበኩላቸውን ድጋፍ ማበርከታቸውን ገልጸዋል።

ሠራዊቱ አገርና ሕዝብ እያገለገለ መኾኑን የገለጹት ብርጋዲየር ጄኔራል ቡልቲ ታደሰ፤ ለአገር እየሠራ ያለን ሠራዊት ከጀርባው በመጠቃቱ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ማዘናቸውን ገልጸዋል። አክለውም አቶ አንዳርጋቸው ለሠራዊቱ ያደረጉትን ድጋር ከልብ አመስግነው፤ ሌሎች ኢትዮጵያውያንም ለሠራዊቱ የሞራል ስንቅ ይኾን ዘንድ ድጋፋቸውን ይሰጡ ዘንድ ጠይቀዋል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ