ሠራዊቱን ለማጠናከር ከ425 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጓል
የሠራዊት ምልመላ በሁሉም ክልሎች ሲደረግ በአዲስ አበባ አልተካሄደም
Ethiopia Zare (ዓርብ ግንቦት 29 ቀን 2000 ዓ.ም. June 6, 2008)፦ ከአዲስ አበባ ውጭ በተለያዩ ክልሎች የሠራዊት ምልመላ የተደረገ ሲሆን፣ ከ425 ሚሊዮን ብር በላይ ለሠራዊት ማጠናከሪያ በሚል ሰበብ ወጭ መደረጉን እንዲሁም ከ2ሺ በላይ የሶማሊያ የሽግግር መንግሥት መከላከያ ሠራዊት አባላት እየሠለጠኑ መሆኑ ተገለጸ።
የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር የ2000 በጀት ዓመት፣ የዘጠኝ ወር የዕቅድ አፈፃፀምን በተመለከተ ባቀረበው ሪፖርት፣ የሱማሊያን የሽግግር መንግሥት ለመደገፍ ለሠራዊቱ የተለያዩ ሥልጠናዎች ተሰጥተዋል።
ቀደም ሲል ለሥልጠና የመጡ 700 ወታደሮችን የያዘ አራት ሻለቃ ጦር ሥልጠናቸውን ጨርሰው ወደ ሱማሊያ የተመለሱ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በ12 ዓይነት ወታደራዊ ሥልጠናዎች 1ሺ 489 ሠልጣኞች ሥልጠና እየወሰዱ ነው።
የሶማሊያ የሽግግር መንግሥት ሠራዊትን አቅም ለማሳደግና ራሱን እንዲችል በሚደረገው ጥረት ሰልጥኖ ሥራ ላይ የተሠማራውና በመሠልጠን ላይ ያለው የሰው ኃይል 2ሺ 189 መሆኑ ተገልጿል።
በተያያዘ የመከላከያ ሚኒስቴር ባለፉት ዘጠኝ ወራት ተተኪ የሰው ኃይል ለማፍራት 10ሺ 683 የአዲስ አባላት ምልመላ ማካሄዱን አስታውቋል። ተተኪ የሰው ኃይል ለማፍራት ምልመላው የተካሄደው በሁሉም ክልሎች እና በድሬደዋ መስተዳድር ሲሆን፣ በአዲስ አበባ ምንም ዓይነት ምልመላ አለመካሄዱን ከሪፖርቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የመከላከያ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ካሣሁን ደንድር ከትናንት በስቲያ ለምክር ቤቱ ባቀረቡት ሪፖርት ላይ እንደገለፁት፣ የኦነግ፣ የአብነግ፣ የአል-እስላሚያ እና የአርበኞች ግንባር የመሣሠሉትን የመመንጠር ሥራ መሠራቱንና የሠራዊቱን አቅም ለማጠናከር ከ425 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የጦር መሣሪያ ግዥ ተፈፅሟል ማለታቸው የተዘገበ ቢሆንም፤ እነዚህ የተቃዋሚ የሽምቅ ተዋጊዎች በአገዛዙ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ እያሳደሩ መሆኑንና አገዛዙ በጦር መሳሪያ ግዥ ብቻ ይሄንን ያህል ገንዘብ ለመፍሰስ መገደዱና ያሳያል ሲሉ እንዳንድ ተንታኞች አስረድተዋል።
በሠራዊቱ ውስጥ ምንም አይነት መተማመን አለመኖሩንና በተለያይ የበላይ አዛዦች ከቅርብ ጊዜ በፊት ለእስር የተዳረጉ ጄኔራሎችና የጦሩ የበላይ ተጠሪዎች ላይ የደረሰው የእስርና የመባረር ተግባር በሠራዊቱ ግዴለሽነትንና የሥነስርዓት ብልሹነትን ከእለት እለት እያባባሰው መገኘቱን እነዚሁ ተንታኞች አክለው ገልጸዋል።