Tesfaye Gessesse

አንጋፋው የኪነጥበብ ባለሙያና መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ተስፋዬ ገሠሠ

በኢትዮጵያ የኪነጥበብ ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ አበርክቷል

ኢዛ (ረቡዕ ታኅሣሥ ፯ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. December 16, 2020)፦ አንጋፋው የኪነጥበብ ባለሙያና መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ተስፋዬ ገሠሠ በ83 ዓመቱ ዛሬ ታኅሣሥ 7 ቀን 2013 ዓ.ም. ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።

መስከረም 17 ቀን 1930 ዓ.ም. (September 27, 1937) በቀድሞው የሐረርጌ ጠቅላይ ግዛት ልዩ ስሙ ጎሮ ጉቱ በሚባለው አካባቢ የተወለደውና በኢትዮጵያ የኪነጥበብ ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ አበርክቶ የነበረው ተስፋዬ ገሠሠ በዘርፉ በቲአትር መምህርነት ለሠላሳ ዓመታት ከማገልገሉ ባሻገር፤ ጸሐፊ ተውኔት፣ የቲአትር አዘጋጅ እና ተርጓሚ በመኾን ጭምር ለበርካታ ዓመታት አገልግሏል።

በቲአትር ተዋናይነት እና በተለያዩ ፊልሞች ላይም በመተወን የሚታወቀው ተስፋዬ ገሠሠ፤ ዕድሜ በተጫጫነው ወቅት ሳይቀር በዚሁ አንቱ በተባለበት ሞያው ተሳታፊ ነበር።

በበርካታ ቲአትሮች ላይ በመሳተፍ የሚታወቀው ተስፋዬ ገሠሠ፤ የሼክስፒር ድርሰት በኾነውና በሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን በተተረጎመው “ሐምሌት” ቲአትር ላይ ከመተወኑም ባሻገር፤ በሌሎች ቲአትሮች በድርሰት በተዋናይነት እና በአዘጋጅነት ሠርቷል።

ተስፋዬ ገሠሠ በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን በጋዜጠኝነት፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የባሕል ማዕከል በኃላፊነት፤ እንዲሁም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቲአትርን በሥራ አስኪያጅነት መምራቱም ይታወቃል።
ረዳት ፕሮፌሰር ተስፋዬ ገሠሠ የሁለት ልጆች (ሴት እና ወንድ) ልጆች አባት የነበረ ሲሆን፤ አያት ለመኾንም በቅቷል። የኢትዮጵያ ዛሬ ዝግጅት ክፍል ለረዳት ፕሮፌሰር ተስፋዬ ገሠሠ ቤተሰቦች፣ ዘመዶች፣ ወዳጆች፣ አፍቃሪዎችና አክባሪዎች መጽናናትን ይመኛል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!