የቀድሞው የቤንሻንጉል ክልል ፕሬዝዳንት አረፉ

የመጀመሪያው የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ያረጋል አይሸሹም
አቶ ያረጋል አይሸሹም ያረፉት በድንገተኛ ሕመም ነው
ኢዛ (ማክሰኞ ኅዳር ፱ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. November 19, 2019)፦ የመጀመሪያው የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ፕሬዝዳንት (ርዕሰ መስተዳድር) አቶ ያረጋል አይሸሹም ትናንት ኅዳር 8 ቀን 2012 ዓ.ም. አረፉ። አቶ ያረጋል በድንገተኛ ሕመም ማረፋቸው ዛሬ ተሰምቷል።
ከቤንሻንጉል ፕሬዝዳንትነታቸው በተጨማሪ የፌዴራል ሕብረት ሥራ ኤጀንሲ ዳይሬክተር በመኾን ሲያገለግሉ መቆየታቸው የሚታወስ ሲሆን፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል በመኾንም አገልግለዋል።
አቶ ያረጋል በፌዴራል መንግሥት በሙስና ተከሰው ታስረው የነበረ ሲሆን፣ ከእስር ከወጡ በኋላ የተከሰሱት ክስ አግባብ አልነበርም በማለት መናገራቸው አይዘነጋም።
አቶ ያረጋል የቤንሻንጉል ርዕሰ መስተዳድር ኾነው ያገለገሉት ከ1987 - 2002 ዓ.ም. ነው። አቶ ያረጋል 51 ዓመታቸው ነበር። (ኢዛ)